ሐምሌ 29 2017 - በኢትዮጵያ በቤት ውስጥ በካይ ጭስ እና ለተበከለ አየር ለረጅም ጊዜ መጋለጥ ለሳንባ ካንሰር ዋና መንስኤ እየሆነ ነው ተባለ
- sheger1021fm
- Aug 5
- 2 min read
በኢትዮጵያ በቤት ውስጥ በካይ ጭስ እና ለተበከለ አየር ለረጅም ጊዜ መጋለጥ ለበርካታ የመተንፈሻ አካላት ህመም እንዲሁም የሳንባ ካንሰር ዋና መንስኤ እየሆነ ነው ተባለ።
በኢትዮጵያ ላለው የሳንባ ካንሰር እና ሌሎች የመተንፈሻ አካል ህመሞች ከትምባሆ እና ተመሳሳይ ምርቶች ተጋላጭነት በተጨማሪ ሌላው መንስኤ የቤት ውስጥ የባዮጋስ ጭስ ብክለት እየሆነ መምጣቱን ጥናት አሳይቷል።
በተለይ ወጣቶች በሳንባ ካንሰር የመጠቃት እድላቸው እየጨመረ መምጣቱ ተነግሯል።
ይህን የሰማው ዛሬ የዓለም የሳንባ ካንሰር ቀን በተመለከተ የሳንባ ካንሰርን ሳይባባስ እና ሳይሰራጭ በምርመራ መለየት ይቻላል በሚል ሀሳብ የጤና ሚኒስቴር፣ ከማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲና የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ጋር በመተባበር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሳምባ ካንሰርን በተመለከተ የተሰሩ ጥናቶች ይፋ በተደረጉበት ጊዜ ተገኝተን ነው።
የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ጋር በመተባበር በተለያዩ መርሀ ግብሮች ከሀምሌ 21 እስከ 25 የተለያዩ የግንዛቤ እና ነፃ የቅድመ ምርመራ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱ ተነግሯል።
ይህ ዓለም ዓለም አቀፍ ቀን በብሪስቶል ማየርስ ስኩዊብ ፋውንዴሽን (BMSF) ድጋፍ ኢትዮጵያ ላይ የሚተገበረው የሳንባ ካንሰር ፕሮጀክት አካል ነው ተብሏል።
የዓለም የሳምባ ካንሰር ቀን በኢትዮጵያ ሲከበር በሳምባ ካንሰር ላይ እየተጠኑ ያሉ የጥናት ግኝቶች ቀርበዋል።
በጥናቶቹ ላይ ተመራማሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎችና ፖሊሲ አውጪዎች በኢትዮጵያ ባለው የሳምባ ካንሰር ስርጭት ላይ ምክክር አድርገዋል።
የሳንባ ካንሰር በዓለም አቀፍ ደረጃ በስፋት ከሚታወቁት የካንሰር ዓይነቶች አንዱ መሆኑንና በካንሰር ምክንያት ለሚከሰት የሞት ምጣኔ ደግሞ በቀዳሚነት እንደሚቀመጥ ተነግሯል፡፡
የሳንባ ካንሰር ህክምና ውጤታማነት ካንሰሩ በታወቀበት ጊዜ ካለው የስርጭት ደረጃ ጋር ይገናኛል፤ ይህም ማለት በሽታው በመጀመሪያ ደረጃ ወይም ሳይዛመት በፊት መለየት ከተቻለ የታካሚውን የህክምና ውጤት በእጅጉ ማሻሻል እንደሚቻል ተጠቅሷል፡፡
በብሪስቶል ማየርስ ስኩዊብ ፋውንዴሽን (BMSF) ድጋፍ የሳምባ ካንሰር ተጋላጭነትን በመፈተሽ የቅድመ ልየታና ክትትል ሥራ ከአምስት ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ፣ኦሮሚያ፣ አማራና አፋር ክልሎች በተመረጡ የጤና ተቋማት ተጀምሯል ሲሉ የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ራሔል አርጋው ተናግረዋል።
በእነዚህ ተቋማት ላይ ግንዛቤ የመፍጠር፣ የጤና ባለሙያዎችን አቅም የማሳደግና ከኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር የተጣጣሙ ሳይንሳዊ ጥናቶችን የመለየት ሥራዎች እንደተከወኑ ተነግሯል።
በኢትዮጵያ የሳምባ ካንሰር ላይ የምርምርና ጥናት ውጤቶች ውስንነት በመኖሩ የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ በዘርፉ ካሉ አካላት ጋር በትብብር እየሰራሁ ነው ብሏል።
በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ የሚልቁት የሳንባ ካንሰር ተጠቂዎች በጣም ዘግይተው ወደ ህክምና ተቋማት እንደሚመጡም ጥናቱ ያሳያል።
ለዚህም የሳንባ ካንሰር ምልክቶች ግንዛቤ አነስተኛ መሆን የቅድመ ምርመራ እና ክትትል ትግበራ በደምብ አለመዳበር ምክንያት ናቸው ተብሏል።
በኢትዮጵያ የሳንባ ካንሰር ምጣኔ እየጨመረ መምጣቱን አመላካች ጥናቶች በመበራከታቸው፤ የሳንባ ካንሰር ቅድመ ምርመራ እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን አጠናክሮ መቀጠል እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
የሳምባ ካንሰር ህመም በሚታወቅበት ጊዜም የካንሰር ደረጃው ስር የሰደደና የተሰራጨ ስለሚሆን ህክምናው አብዛኛውን ጊዜ ውጤታማ አይሆንም ተብሏል።
በኢትዮጵያ ለጡትና የማህፀን ጫፍ ካንሰር እንደሚደረገው ማህበረሰብ አቀፍ የካንሰር ቅድመ ምርመራ ሁሉ ለሳንባ ተግባራዊ አለመደረጉ ችግሩን አባብሶታል ሲል የኢትዮጵያ ቶራሲክ ሶሳይቲ ተናግሯል።
ሲጋራና ሺሻ ማጨስ፣ ለከባድ ጭስና የተበከለ አየር ተጋላጭነት፣ በሥራ ቦታ ለመርዛማ ብናኞች (ንጥረ ነገሮች) መጋለጥና ስር የሰደደ የመተንፈሻ አካላት በሽታ ታማሚ መሆን በጥናት የተለዩ የሳምባ ካንሰር አጋላጭ መንስኤ ሆነው ተጠቅሰዋል።
ቅድመ ምርመራ፣ የሕክምና ክትትል ማድረግ፣ የባህሪ ለውጥ በሽታውን በመከላከልና ህክምናው በጊዜ ውጤታማ እንዲሆን ያደርጋሉ መባሉን ሰምተናል።
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyu.com/ycxjmm3s












Comments