ሐምሌ 16 2017 - ''127,000 የህብረት ስራ ማህበራት አሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ በስራ የተገኙት ግን ወደ 89,000 አካባቢ ናቸው''
- sheger1021fm
- Jul 23
- 1 min read
ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙ አብዛኞቹ የህብረት ስራ ማህበራት ከብዙ ዓመታት በፊት መቶ ብር እና ከዚያ በታች በሆኑ ትናንሽ የግለሰቦች የገንዘብ መዋጮ የተቋቋሙ ናቸው።
ተግባራቸው እንደ ተደራጁበት ዓላማ ቢለያይም የአብዛኞቹ የምርት አቅርቦትን በማሳደግ ገበያን ማረጋጋት ነው።
ይህን ሲያደርጉ አምራቹ ትክክለኛውን ዋጋ ያገኛል፤ ሸማቹም ጥራት ያለው ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ ይገዛል ተብሎ ይታሰባል።
ይህን ዓላማ ከማሳካት አንፃር ምንም አልሰሩም ባይባልም የታሰበውን ያህል ናቸው ለማለትም እንደሚከበድ የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን ይናገራል።
ኮሚሽኑ እንደሚለው የብቃት እና የተወዳዳሪነት ማነስ፣ የሃብት ብክነትና ዘረፋ እንዲሁም እንደ ፋይናንስ እጥረት ያሉ ችግሮች በማህበራቱ ላይ ታይተዋል።

እነዚህን እና መሠል የማህበራቱን ችግሮች ለመፍታት ደግሞ ዘርፉን ሪፎርም ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ተገልፆ ስራ ተጀምሯል።
ስራው ማህበራቱ በርግጥም አሉ ወይ? የሚለውን ከመለየት እንደጀመረ የኢትዮጵያ የህብረት ስራ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ ነግረውናል።
127,000 የህብረት ስራ ማህበራት አሉ ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ በመለየቱ ስራ የተገኙት ግን ወደ 89,000 አካባቢ ናቸው ብለዋል።
የህብረት ስራ ማህበራት ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ እንደማይሆኑ የነገሩን አቶ ሺሠማ በደረጃ እንከፍላቸዋልን ብለዋል። ስራው መጀመሩንም ነግረውናል።
በደረጃቸው መሰረት የህብረት ስራ ማህበራቱ የምስክር ወረቀት እንደሚያገኙ እና የሚሰጡት አገልግሎትም ይህንኑ መሰረት ያደረገ እንደሚሆን ተነግሯል።
በወጣው ደረጃ ውስጥ መካተት ያልቻሉት እንደገና ተደራጅተው እንዲመጡ ዕድል ይሰጣቸዋል ያሉን አቶ ሺሠማ የመጨረሻው እርምጃ እንዲፈርሱ መወሰን እንደሆነ አክለዋል።
የህብረት ስራ ማህበራት በአደጉትም ሆነ እያደጉ ባሉ ሀገራት ይገኛሉ የሚሉት አቶ ሺሰማ አስፈላጊነታቸው ላይ እዚህም ጥያቄ እንደሌለ ተናግረዋል።
ሪፎርሙ ሁሉንም ህብረተሰብ በሁሉም ስራ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማስቻል ግብ ያለው ብቻ እንደሆነ ማወቅ ይገባል ብለዋል።
ሪፎርሙ የህብረት ስራ ማህበራቱ ጠንካራ አደረጃጀት እና አመራር እንዲኖራቸው ያስችላል ተብሏል።
የገበያ ድርሻቸውን እና ተጽዕኗቸውን የሚያሳድግ እንደሚሆንም ተጠቅሷል።
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s











Comments