ሐምሌ 15 2017 - አዲስ አበባ፤ ከቡራዩ እስከ አንቆርጫ ዙሪያዋን የከበባትን የባህርዛፍ ደን አንስታ በሀገር በቀል ዛፎች ለመተካት አስባለች
- sheger1021fm
- Jul 22
- 1 min read
አዲስ አበባ፤ ከቡራዩ እስከ አንቆርጫ ዙሪያዋን የከበባትን የ #ባህርዛፍ ደን አንስታ በሀገር በቀል ዛፎች ለመተካት አስባለች።
በቀን እስከ 200 ሊትር ውሃ የሚጠቀመው የባህር ዛፍ ተክል የከተማውን የውሃ ምንጭ እያደረቀ ለከፍተኛ የውሃ እጥረት ምክንያት እየሆነ ነው ተብሏል።
በአዲስ አበባ እየተገነባ በሚገኘው ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ መናፈሻ የሚደርሰው የ21.5 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳር ፕሮጀክት ከሚሰሩ ስራዎች አንዱ በተለያየ ምክንያት ህይወት አልባ የሆኑት የአዲስ አበባ ወንዞች መልሰው ነብስ እንዲዘሩ ማድረግ ነው ተብሏል።
አቶ ዋለልኝ ደሳለኝ የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስፈጻሚ እና ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ በግንባታ ላይ ያለው የአዲስ አበባ የወንዝ እና የወንዝ ዳርቻ ኮሪደር ልማት ምክትል አስተባባሪ ናቸው።

ከእርሳቸው እንደሰማነው በቀደመው ጊዜ ለአዲስ አበቤ የማገዶና የቤት መስሪያ ፍላጎቱን እንዲሸፍን ታስቦ በእንጦጦ እና ዙሪያው የተተከለው የባህር ዛፍ ዛሬ ለከተማው ወንዞች ውሃ አልባ መሆን አንዱ ምክንያት ሆኗል።
ይህንን በሀገር በቀል ዛፍ ለመተካት በእንጦጦ ዙሪያ፣ የጉለሌ እፅዋት ማዕከል የመተካት ስራ ከጀመረ ከ13 ዓመት በላይ እንደሆነው እና እስካሁን 704 ሄክታር መሬትን በሀገር በቀል ዛፍ መተካቱን የተናገሩት አቶ ዋለልኝ፣ በወንዝ ዳር ፕሮጀክቱ ምክንያት እኛም በእንጦጦ ተራራ ላይ በ3 ዓመት ጊዜ ውስጥ 438 ሄክታር በሬትን ከባህር ዛፍ ነፃ አድርገን በምትኩ ሀገር በቀል ዛፍ ለመትከል ስራ ጀምረናል ብለዋል።
በሺዎች ሄክታር የሚቆጠረውን አዲስ አበባን ዙሪያዋን የከበበውን የባህር ዛፍ ሙሉ ለሙሉ ለመተካት ግን ረጅም ጊዜ ሊወስድ ይችላል ብለዋል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ቴዎድሮስ ወርቁ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s








