ሐምሌ 11 2017 - ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ 17ኛው ባለብዙ ዘርፍ አውደ ጥናት አካሄደ።
- sheger1021fm
- Jul 18
- 1 min read
ዩኒቨርሲቲው በየዓመቱ በሚያካሄደው የባለብዙ ዘርፍ አውደ ጥናት ጉባኤ ላይ የሚቀርቡ የምርምር ስራዎች በሚገባ ተሰንደው ለፖሊሲ አውጪዎችና ለሌሎችም ለሚመለከታቸው አካላት እየሰጠሁ ነው ተብሏል፡፡
ባለፉት 17 ዓመታት ይህ ጉባኤ ሲካሄድ ነበር በዚህ አውደ ጥናት ላይ የቀረቡ ጥናታዊ ፅሁፎች በተገቢው መንገድ ከተመረመሩ በኋላ ተሰንደው ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርሳቸው ተደርጓልም ተብሏል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ወንድወሰን ታምራት(ዶ/ር) በዚህ ጉባኤ የሚቀርቡ ጥናቶች ዋነኛ መስፈርታቸው ሀገሪቱ በወቅቱ ከያዘቻቸው እቅዶች ጋር የሚሄዱ መሆናቸው ልዩ ያደርጋቸዋል ብለዋል።
የምርምር ስራዎቹ ሲመረጡም ተግባራዊነት ያላቸውና የሚያመጡት ለውጥና ተፅዕኖ ትኩረት ይደረግባቸዋል ሲሉ ጠቅሰዋል።

በዘንድሮው ዓመት በተደረገው 17ተኛው አውደ ጥናት የፋይናንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ አይሲቲ፣ የዋጋ ግሽበት እና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ የተሰሩ ጥናትና ምርምሮች በአውደ ጥናቱ ቀርበዋል።
ከዚህ ቀደም የሚሰሩ ጥናትና ምርምሮች ከተሰሩ በኋላ ወደ ተግባር ሳይወርዱ መደርደሪያ ላይ ይቀሩ ነበር ያሉን የቅድስተ ማርያም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ወንድወሰን ታምራት(ዶ/ር) ሙሉ ለሙሉ ባይባልም አሁን ግን ጥናቶች ከተሰሩ በኋላ ወደተግባር እየተቀየሩ ነው ብለዋል፡፡
በዘንድሮው ዓመት ከመደወላቡ፣ አርባ ምንጭ፣ ወልድያ እና ከቅድስተ ማርያም ዩኒቨርስቲ የተውጣጡ አጥኚዎች ስራዎቻቸውን አቅርበዋል።
የግልም ሆነ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚደረጉ ምርምሮች ላይ በጋራ መስራት አለባቸው የተባለ ሲሆን ይህም የተሻለ ስራ ለመስራት ይረዳል ተብሏል።
በረከት አካሉ








