ሐምሌ 10 2017 - በጎንደር ከተማ የሚገኙ የአጼ ፋሲልና ሌሎች ነገሥታት ቤተ መንግስቶች ከመፍረስ ድነው ዳግም እየታደሱ ነው
- sheger1021fm
- Jul 17
- 1 min read

ባለፈው አመት የተጀመረው ከፊሉ የእድሳት ስራ እየተጠናቀቀ ነው ተብሏል፡፡
በተለያየ ቦታ ተበታትነው የሚገኙ የቤተ-መንግስቱ ታሪካዊ ቅርሶች እንዲመለሱም ጥያቄ ለማቅረብ ዝግጅት እየተደረገ ነው ተብሏል።
ታሪካዊው የአጼ ፋሲል ቤተ መንግስት በቀደመው ጊዜ በመሐዲስቶች መቃጠሉ እንዲሁም ጣልያን አምስት ዓመት ሲቆይ የጦር ካምፕ አድርጎት ስለነበር እንግሊዞች ለማስለቀቅ ሲሉ ቦምብ ጥለውበት መጎዳቱ ይነገራል።
ከ40 ዓመት ገደማ በፊት መጠነኛ ጥገና ተደርጎለት የነበረው ቤተ መንግስቱ ከዛን ጊዜ ወዲህ ግን ምንም ጥገና ባለማግኘቱ እጅግ ተጎሳቁሎ ከፊሉም መፍረስ ጀምሮ እንደነበር ይታወቃል።
ወ.ሮ ደብሬ የውሃላ የከተማው ምክትል ከንቲባ ናቸው።
እሳቸው እንደነገሩን ቅርሱ መፈራረስ በመጀመሩ የተወሰነው ክፍል ብረት ተደግፎ እንዲቆም የማድረግ ጥረት ሁሉ ሲደረግ ነበር።
ባለፈው ዓመት መንግስት በወሰነው መሰረት ግን በግቢው ያሉ ቤተ-መንግስታትና ሌሎች ታሪካዊ ሀብቶች የቀደመ መልካቸው ሳይቀየር እንዲታደሱ እየተደረገ ነው ብለዋል።
ባለፈው ዓመት የተጀመረው ከፊሉ የቤተ-መንግስቱ እድሳት ስራ እየተጠናቀቀ መሆኑን ነግረውናል።
ቅርሱን የማደስ ስራው ቢአይካ ኮንስትራክሽን በተባለ የግንባታ ተቋም እየተሰራ መሆኑ ተነግሯል።
የጎንደር አስጎብኚዎች ማህበር አባልና የፕሮጀክቱ መረጃ ሰጪ የሆኑት አቶ ዳዊት አጠቃ እንደነገሩን አሁን የአፄ ፋሲል ቤተ-መንግስትን ጨምሮ የመጀመሪያው ምዕራፍ የሚበዛው ስራ ተጠናቋል።
በሁለተኛው ምዕራፍ በግቢው ያሉ የሌሎች ሶስት ቤተ-መንግስታት እድሳት ስራም ይሰራል ብለዋል።
ቴዎድሮስ ወርቁ
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….. 👇👇👇👇👇












Comments