የሁለት ወር ጨቅላ ህፃን ለቀናት ከተጣለበት የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ ሞቶ መገኘቱን የአዲስ አበባ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ተናገረ፡፡
ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥቅምት 2 ቀን 2017 ዓ.ም በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ሃይሌ ጋርትመንት አካባቢ ባለ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ ውስጥ የሁለት ወር ህፃን ሞቶ መገኘቱን የነገሩን የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ናቸው፡፡
እርሳቸው እንደሚሉት ህፃኑ ከአካባቢው ራቅ ባለ ወንዝ ተጥሎ የቆየና ተገፍቶ ሃይሌ ጋርመንት አካባቢ ካለ አንድ የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦ የደረሰ ነው፡፡
በወላጆቹ ተጥሎ እንደሚሆን ግምት እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ ንጋቱ የአደጋው መንስኤ በፖሊስ እተጣራ መሆኑን ነግረውናል፡፡
ባለፈው ዓመት 2016 ዓ.ም በተመሳሳይ 3 ጨቅላ ህፃናት በመፀዳጃ ቤት ተጥለው ማግኘታቸውንና ይህ ጭካኔ ተሞላው ድርጊት የሚፈፀመው በወላጅ እናቶች እንደሆነም ጠቅሰዋል፡፡
ድርጊቱ እናቶች ከእርግዝና ጀምሮ ከሚያሳልፉት አስጨናቂ ጊዜ ጋር እንደሚገናኛ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲናገሩ ይደመጣል፤አቶ ንጋቱም ይህ ጉዳይ እየተደጋገመ ነው፣ ባለሙያዎቹ በጉዳዩ ላይ በርትተው ቢሰሩ ይላሉ፡፡
በሌላ በኩል በቦሌ ክፍለ ከተማ ሚሊኒየም አዳራሽ አካባቢ የጉድጓድ ውሃ የሚያወጡ ሰዎችን ለማገዝ ወደ ጉድጓድ የገባ እድሜው 35 ዓመት የሆነ የጥበቃ ሰራተኛ ህይወቱ አልፏል፡፡
በተጨማሪም በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ሃያት አካባቢ እድሜው 40 ዓመት የተገመተ ግለሰብ ወንዝ ውስጥ ህይወቱ አልፎ ተገኝቷል፡፡
በተያያዘም በሸገር ከተማ አሸዋ ሜዳ አካባቢ በአንድ ሆቴል ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ በሆቴሉ የመኝታ ክፍል ተኝቶ የነበረ የ38 ዓመት ግለሰብ በአደጋው ህይወቱ ሲያልፍ፣ በሁለት የእሳት አደጋ ሰራተኞች ላይም ጉዳት ደርሷል፡፡
የአደጋዎቹ መንኤዎች በፖሊስ እየተጣራ መሆኑን ባለሙያው ነግረውናል፡፡
እነዚህ 4ቱም አደጋዎች የተከሰቱት ከዓርብ ጥቅምት 1 እስከ እሁድ ጥቅምት 3 2017 ዓ.ም ሲሆን በአደጋዎቹ 4 ሰዎች ሲሞቱ በ3 ሰዎች ላይ ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት መድረሱን ከአቶ ንጋቱ ማሞ ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Comments