ግንቦት 22 2017 - የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች በማራኪ እና አሳሳች በሆኑ ስልቶች ወጣቶችን አማልለው በሱስ እንዲጠመዱ እያደረጉ መሆኑ ተነገረ
- sheger1021fm
- May 30
- 2 min read
የትምባሆ ኢንዱስትሪዎች በማራኪ እና አሳሳች እንዲሁም ሳቢ በሆኑ ስልቶች ወጣቶችን አማልለው በሱስ እንዲጠመዱ እያደረጉ መሆኑ ተነገረ፡፡
ኢንዱስትሪዎቹ፤ ቄንጠኛ ዲዛይኖች፣ ማራኪ ቀለሞች፣ አሳሳች ንድፎች፣ ጣዕማቸውን የሚያጣፍጡ ቅመሞች እና ንጥረ ነገሮችን በመጨመር በዲጅታል ሚዲያ እና በሌሎች መገናኛ ዘዴዎች ወደ ወጣቶች እያሰራጩ ይገኛሉ ተብሏል፡፡
የተጠቀሱት እና ሌሎች ዘዴዎች ያለማቋረጥ በመጠቀምም የትምባሆ ጎጂነትን ስልታዊ በሆነ መልኩ በመደበቅ ህጻናት እና ወጣቶችን እያማመሉ በሱስ እንዲጠመዱ እያደረጉ ነው መባሉን ሰምተናል፡፡
የአለም ትምባሆ የማይጨስበት ቀን በኢትዮጵያ ለ33ኛ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ38ኛ ጊዜ ነገ ግንቦት 23 2017 ይከበራል፡፡
እለቱን አስመልክቶም የኢትዮጵያ የምግብና መድሃኒት ባለስልጣን ከሌሎች ከሚመለከታቸው ጋር በመሆን ዛሬ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥቷል፡፡
በነገው እዕት ለሚከበረው የዓለም ትንባሆ የማይጨስበት ቀንም “በትምባሆ እና በኒኮቲን ምርቶች ላይ፤ የትምባሆ ኢንዱስትሪ አሳሳችና ድብቅ ስልቶችን በማጋለጥ ወጣቶችን እንታደግ” የሚል መሪ ቃል ተመርጦለታል፡፡
የኢትዮጵያ ምግብና መድሀኒት ባለስልጣን የአጮሾች ቁጥር ለመቀነስ እና በሰዎች ላይ የሚያደርሰውን ጉዳትም ዝቅ ለማድረግ ለመቀነስ የተለያዩ የግንዛቤ መስጫ እና የቁጥጥር ስራዎችን እየሰራሁ ነው ሲል ተናግሯል፡፡

ባለስልጣኑ ባለፉት 8 ዓመታት የሀገሪቱን ተጠቃሚዎችን በተመለከተ ከሌሎች ከሚመለከታቸው ጋራ ሁለቴ (እ.ኤ.አ በ2016 እና በ2024) የዳሰሳ ጥናት አድርጊያለሁም ብሏል፡፡
ከ8 ዓመት በፊት የተጠናው ጥናት በኢትዮጵያ የትምባሆ ተጠቃሚዎች ቁጥር 5 በመቶ የነበረ ሲሆን ከአንድ ዓመት በፊት የተጠናው ጥናት ደግሞ የተጠቃሚዎች ቁጥር በአንፃራዊነት ቀንሶ 4.6 በመቶ ሆኖ ታይቷል ብሏል ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ፡፡
በ2016ቱ ጥናት 1.2 በመቶ የነበረው የሴት ትምባሆ አጫሾች ቁጥርም በ2024ቱ ጥናት ወደ 0.4 በመቶ ዝቅ እንዳለም ተነግሯል፡፡
በዓለም ዙሪያ 1.3 ቢሊዮን የትምባሆ ተጠቃሚዎች እንዳሉና ከ8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ በዚሁ የተነሳ ህይወታቸውን እንደሚያጡ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡
በትምባሆ ምክንያት ህወይታቸውን ከሚያጡ ከእነዚህ መካካልም 1 ሚሊዮን ገደማዎቹ የትምባሆ ተጠቃሚ ሳይሆኑ በአካካቢያቸው ሌሎች ሲጠቀሙ በሚያገኛቸው የትምባሆ ጭስ የተነሳ ነው ተብሏል፡፡
በትምባሆ ቅጠል ውስጥ ከ7,000 በላይ ኬሚካሎችን በውስጡ እንደሚይዘና ከእነዚህ ኬሚካሎችም አብዛኞቹ ጎጂ ሲሆኑ በተለይ 70 የሚሆኑ ካንሰር አምጪ ኬሚካል መሆናቸውን ተነግሯል፡፡
ሲጋራ ማጨስ እና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን መጠቀም በሱስ ለመያዝ፣ ለአደገኛ የሳንባ በሽታ፣ ለካንሰር፣ ለልብ በሽታ መዳረግ፣ ለፅንስ መጎዳት፣ በሚጨስበት አካባቢ በሚኖሩ እና በማያጨሱ ሰዎች ላይ ጭምር ከፍተኛ የሆነ የጤና መታወክ እና ሌሎችንም ጉዳቶች እያስከተለ ይገኛል ተብሏል፡፡
በአለም ላይ ካሉት 1.3 ቢሊዮን የትምባሆ ተጠቃሚዎች 80 በመቶ የሚያህሉት የሚኖሩት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት መሆኑን እና ከጤና ጉዳቱ ባሻገር፤ የቤተሰብ ወጪን እንደ ምግብ እና መጠለያ ካሉት ከመሰረታዊ ፍላጎቶች ወደ ትምባሆ በማዞር ለድህነት አስተዋፅኦ እንደሚደርግም ከጥናቶች ተመልክተናል፡፡
ኢትዮጵያ በ2005 ዓ.ም በአለምጤና ድርጅት አማካኝነት የተዘጋጀውና የትምባሆ ተጠቃሚዎችን ቁጥር ለመቀነስ ታሳቢ ያደረገው እና ዝርዝር ድንዳጌዎችን የያዘ ዓለም አቀፍ የትምባሆ ቁጥጥር ማዕቀፍ ስምምነት ፈርማና በህጓ አካትታ እየሰራችበት እንደሆነ የምግብና መድሀኒት ባለስልጣን አስረድቷል፡፡
ይህ ስምምነት በትምባሆ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ቀረጥ መጣል፣ በምርቶቹ ማሸጊያ ላይ ጎጂነቱን በምስል በተደገፈ መልኩ ማሳየት እንዲሁም ማስታዊያዎችን ሙሉ በሙሉ ማገድ የትምባሆ አጫሾችን ለመቀነስ እንደ መፍትሄ ያስቀምጣል፡፡
በኢትዮጵያ፤ የተከለከለ ይዘት ያለው ትምባሆ፣ ሺሻ፣ የኤልክትሮኒክ ኒኮቲን መስጫ መሳሪያ ወይም ሌላ ተመሳሳይ ምርት ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባ፣ ያመረተ፣ ያከማቸ፣ ያከፋፈለ እንዲሁም የሸጠ ሰው የተገኘ እንደሆ እስከ ሶስት ዓመት እስር እና ሁለት መቶ ሺህ ብር ድረስ እንደሚቀጣ በህግ ተቀምጧል፡፡
አንድ ትምባሆየሚያጨስ ሰው ከማያጨስ ሰው ጋር ሲነፃፀር በህይወት የመቆየት እድሜው ቢያንስ በ10 ዓመት ያጥራል መባሉንም ሰምተናል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comentarios