top of page

ታህሳስ 6፣ 2015- በታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተጠየቀ


በታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት ዙሪያ የሚስተዋሉ ችግሮች አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተጠየቀ።


የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በታለመለት የነዳጅ ድጎማ ስርዓት አፈፃፀም ዙሪያ ያስጠናውን ጥናት ዛሬ በአዳማ ከተማ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ይፋ አድርጓል።


የጥናቱ ውጤት እንዳሳየው የነዳጅ ድጎማ አሰራሩ የተለያዩ ጠንካራ እና ደካማ ውጤቶች ታይተውበታል።


የነዳጅ ብክነትን መቀነሱ እና ተጨማሪ ገቢ ለመንግስት ማስገኘቱ የድጎማ ስርዓቱ ጠንካራ ጎኖች ተብለው ከተነሱት መካከል ናቸው።


የድጎማ አሰራሩ በ1 ወር ብቻ 1 ቢሊየን ብር ግምት ያለው ነዳጅ ከብክነት እንዲድን አግዟል የተባለ ሲሆን ወደ 3.5 ቢሊየን ብር ግምት ያለው ገቢ ለመንግስት አስገኝቷል ተብሏል።


በድጎማ ስርዓቱ አፈፃፀም ዙሪያ ታይተዋል ከተባሉ ችግሮች መካከል ደግሞ አንዳንድ ማደያዎች የነዳጅ እጥረት የተፈጠረ በማስመሰል በህገወጥ መንገድ በእጥፍ ዋጋ ነዳጅ ይሸጣሉ የሚለው ይገኝበታል።


በተሽከርካሪዎች ላይ ያልነበረ የነዳጅ ማጠራቀሚያ ጋን ወይም ሳልቫቲዮ በመግጠም ድጎማው ለማይመለከተው ወገን ነዳጅ መቅዳት የሚለውም ሌላው ነው።


በአንዳንድ ማደያዎች በቴክኖሎጂ አሰራር ወይም ቴሌ ብር ለመሸጥ ፍላጎት ማጣት ይታያልም ተብሏል።


ስልጣናቸውን ተገን አድርገው ቤተሰቦቻቸውን በህገወጥ የነዳጅ ንግድ የሚያሳትፉ የመንግስት ተሿሚዎች አሉም ነው የተባለው።


በአሽከርካሪዎች በኩል ደግሞ የድጎማ ስርዓቱ ተጠቃሚ ሆነው ለህብረተሰቡ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ በኮንትራት ስራ ላይ የተሠማሩ እንዳሉ ተጠቅሷል።


ነዳጅ በድጎማ እየገዙ በመንግስት ከተቀመጠው ታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ እንዳሉም ተነግሯል።


በነዳጅ ድጎማ አሰራር ዙሪያ የሚታዩ እነዚህ እና መሠል ችግሮች አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተጠይቋል፡፡


ንጋቱ ረጋሳ


ሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2024 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page