ሰኔ 24 2017 - የመንግስት የወጪ ፍላጎት በገቢ አቅሙ መሸፈን አለበት የሚል ጠንካራ አቋም መያዙን የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ተናገሩ።
- sheger1021fm
- Jul 1
- 1 min read
ሚኒስትሩ በ2018 የፌዴራል መንግስት ረቂቅ በጀት ዙሪያ ዛሬ ከህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ለተነሱ የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል።
የ2018 የፌዴራል መንግስት ጠቅላላ ወጪ በጀት 1.93 ትሪሊየን ብር ሆኖ መዘጋጀቱ ይታወሳል።
ከተያዘው አጠቃላይ በጀት 1.2 ትሪሊየን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 415.2 ቢሊየን ብር ለካፒታል ወጪ፣ 315 ቢሊየን ብር ለክልሎች የበጀት ድጋፍ እና 14 ቢሊየን ብር ለክልሎች የዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ የተደለደለ እንደሆነ ተነግሯል።
ለአመቱ ከተያዘው 1.93 ትሪሊየን ብር ውስጥ 1.23 ትሪሊየን ብር ታክስ እና ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች ይሰበሰባል ተብሎ ግብ ተቀምጧል።
ለዓመቱ በተዘጋጀው ረቂቅ በጀት ዙሪያ በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ዛሬ ውይይት ተካሂዷል።
የምክር ቤቱ አባላትም የተለያዩ ጥያቄዎችን በረቂቅ በጀቱ ዙሪያ ማብራሪያ ለመስጠት ለተገኙት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ አቅርበዋል።

ከቀረቡ ጥያቄዎች አንዱ ከካፒታል በጀቱ ይልቅ እየጨመረ ያለው አስተዳደራዊ ወጪው ነው። ይሄ እንዴት ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣት ያስችላል? የሚል ነው።
ለጥያቄው ምላሸ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ለመደበኛ ወጪ ከተመደበው በጀት የዕዳና ማህበራዊ አገልግሎት ወጪዎች ሲቀነሱ እንዲያውም የሚበልጠው የካፒታል በጀቱ ነው ብለዋል።
በነባር የታክስ ህጎች ላይ ማሻሸያ እንደሚደረግ ተነግሯል ህብረተሰቡ ግን ቀደም ብለው የተደረጉ የታክስ ማሻሻያችም ተጽዕኖ እንዳሳደረቡት እየገለጸ ነው፤ ይሄስ እንዴት ይታያል? የሚል ጥያቄም ተነስቷል።
ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በበኩላቸው የመንግስት የወጪ ፍላጎት በገቢ አቅሙ መሸፈን አለበት የሚል ጠንካራ አቋም መያዙን ተናግረዋል።
በነዳጅ ላይ ይጣላል የተባለው ተጨማሪ እሴት ታክስም ይሰጥ የነበረውን ድጎማ የሚያስቀር አይደለም ወይ? የሚል ጥያቄም በእንድ የምክር ቤት አባል ቀርቧል።
ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ በሰጡት ምላሽ ድጎማም መሰጠት ያለበት በተጠናና በታለመለት መንገድ ነው ብለዋል።
ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ሌሎች ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ…… https://www.mixcloud.com/ShegerFM/ty/
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments