ሐምሌ 15 2017 - ‘’ግድቡ ከኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ውጪ ‘እኔ ነኝ የገነባሁት’ የሚል አካል ማስረጃ ያቅርብ’’
- sheger1021fm
- Jul 22
- 2 min read
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በመንግስትና በህዝብ ገንዘብ መገንባቱን የግድቡ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ፅ/ቤት ማረጋገጫ ሰጠ፡፡
''ግድቡ በእኔ ገንዘብ ነው የተገነባው የሚል ሌላ አካል ካለ ማስረጃ ያቅርብ'' ሲል ፅ/ቤቱ ጠይቋል፡፡
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ስራዎች አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጠው የማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤቱ፤ ‘’ግድቡ የተሰራው በእኛ ገንዘብ ነው’’ በሚል በአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ተደጋግሞ መነገሩን በተመለከተ በሰጠው ምላሽ ግድቡን ከኢትዮጵያ መንግሰትና ህዘብ ውጪ እኔ ነኝ የሰራሁት የሚል አካል ካለ መረጃ ያቅርብ ብሏል።
ግድቡ ላለፉት 14 ዓመታት የተገነባው ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በተዋጣ ገንዘብ መሆኑን እንዲህ ዓይነት የተሳሳተ መረጃ ለሚያሰራጩ አካላት ማስረገጥ እንወዳለን ሲሉ የማስተባበሪያ ፅህፈት ቤቱ ምክትል ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ፍቅርተ ታምር አስረድተዋል።
ስለ ግድቡ በፕሬዝዳንት ትራምፕ ተደጋግመው በሚነገሩ ሃሳቦች ላይ በፅህፈት ቤቱ ምላሽ ያልተሰጠው በዲፕሎማሲ የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ ነው ብለዋል።

ዲፕሎማሲ የራሱ አካሄድ እንዳለው የጠቆሙት ምክትል ዳይሬክተሯ በዲፕሎማሲው የተሄደበት ርቀት ወደፊት ሊገለፅ እንደሚችል ጠቁመዋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው ግብፆች የአባይን ውሃ ለብቻቸው ለመጠቀም ያላቸውን ዘመናትን ያስቆጠረ ፍላጎት አስታውሰዋል።
ከዚህ ፍላጎታቸው በመነሳት በሃገር ውስጥም ይሁን በውጭ ብቸኛ ተጠቃሚነታቸውን የሚያስቀጥልላቸውን አካል ለማግኘት የማያደርጉት ጥረት የለም፣ የትራምፕን ንግግርም ከዚህ አንፃር ነው የምንመለከተው ብለዋል።
ማንም እየተነሳ እኔ ነኝ የገነባሁት ቢል ምንም ማምጣት አይችልም፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በመስከረም ወር ይመረቃል፤ እንዳይመረቅ ምክንያት ለመሆን የሚሞክር አይጠፋም ነገር ግን ምንም የሚያሰጋ የፀጥታ የሁኔታ የለም ተብሏል።
ግድቡን አስመልክቶ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለ3 ያህል ጊዜ ግድቡ በአሜሪካ ገንዘብ እንደተገነባ ሲናገሩ ቆይተዋል።
ይሁንና በሁሉም ንግግራቸው ወቅት ሃገራቸው መቼ ምን ያህል ገንዘብ እንደሰጠች አልጠቀሱም።
በኢትዮጵያ በኩል ምላሽ እንዲሰጥ ሲጠየቅ ቆይቶ በዛሬው እለት በፅህፈት ቤቱ በኩል የፕሬዝዳንቱ ንግግር ሃሰት መሆኑና ግድቡን ገነባን ካሉም መረጃ ያምጡ የሚል ምላሽ ተሰጥቷል።
የገቢ ማሰባሰቢያ ስራዎች ቀጥለዋል ያለው ፅህፈት ቤቱ በ2017 ዓመት ብቻ ከ1.7 ቢሊዮን ብር በላይ ከህዝቡ መሰብሰብን ሲናገር ሰምተናል።
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
Comentarios