top of page

የባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 157.2 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ተናገረ ።

  • Jul 31
  • 2 min read

ሐምሌ 23 2018


የባህር ትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 157.2 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማግኘቱን ተናገረ ።


ከታክስ በፊት የተገኘው ትርፍም 28.2 ቢሊየን ብር መሆኑ ተነግሯል።


በመካከለኛው ምስራቅ እና በቀይ ባህር ዙሪያ ያለው ጦርነትና ውጥረት ለስራው ፈተና እንደነበር፣ የነዳጅ እጥረትም እንደልብ ለመንቀሳቀስ መቸገርን ጨምሮ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ፈተና እንደነበሩ አስረድቷል።

የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አብዱልበር ሸምሱ የተቋሙን የ2018 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ በተመለከተ ዛሬ ከሰዓት ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።


ዋና ስራ አስፈፃሚው ዓመቱ ለዘርፉ ፈታኝና ከባድ ጊዜ ቢሆንም በብዙ መለኪያዎች ግን የተሻለ ሊባል የሚችል ስራ የተሰራበት እንደነበር ጠቁመዋል።


በበጀት ዓመቱ ተቋሙ በአጠቃላይ 7.04 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ጭነት ማጓጓዝ መቻሉን ተናግረው፣ ከዚህ ውስጥ 5 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶኑ ከኮንቴይነር ውጪ የሆነ ጭነት፣ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶኑ ደግሞ የኮንቴይነር ጭነት እንደሆነ አስረድተዋል።


ከዚህ ጭነት ውስጥ 1.1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶኑ ጭነት የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ባሉት የራሱ 10 መርከቦች የተጓጓዘ መሆኑን አብራርተዋል።


በየዓመቱ ከውጪ ተገዝቶ የሚገባ የአፈር ማዳበሪያን የማጓጓዝ ሀላፊነት ያለበት ተቋሙ፣ በበጀት ዓመቱ 2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ አጓጉዞ ማስገባቱን ጠቅሷል።


ጅቡቲ ወደብ የደረሰውን ማዳበሪያ 26 በመቶውን በባቡር፣ ቀሪውን 74 በመቶ በጭነት ተሽከርካሪዎች ወደ መጨረሻ መዳረሻቸው ማድረሱን አስታውሷል።


የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ በበጀት ዓመቱ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ካሉት 10 መርከቦች በተጨማሪ 47 መርከቦችን በመከራየት እንዲሁም ከ7 መሰል የመርከብ ድርጅቶች (ላይነርስ) ጋር በመተባበር ስራውን መስራቱን ተናግረዋል።


ጭነትን ከወደብ ወደ ደረቅ ወደቦችና ወደ መጨረሻ መዳረሻቸው ለማጓጓዝም 665 የራሱን ከባድ የጭነት ተሽከርካሪዎች እንዲሁም 3,643 ከተቋሙ ውጪ ያሉ የጭነት ተሽከርካሪዎችን በማሰማራት ስራውን መከወን ተችሏል ተብሏል።


በበጀት ዓመቱ ተቋሙ ከሰራው ስራ 157.2 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማስገባት የቻለ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ ከታክስ በፊት የተገኘው ትርፍ 28.2 ቢሊዮን ብር መሆኑ ተነግሯል።


በበጀት ዓመቱ የተገኘው ገቢም ከእቅዱ በላይ 108.5 በመቶ አፈፃፀም ያሳየ መሆኑን ያብራሩት ስራ አስፈፃሚው፣ ቀድሞ ታቅዶ የነበረው 144.9 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ ገቢ ማስገባት እንደነበር ተናግረዋል።


ዓመቱ በመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት እና በቀይ ባህር ዙሪያ ባለ ውጥረት ፈታኝ እንደነበር ያስረዱት ሀላፊው፣ ተቋሙ ካሉት አስር መርከቦች "ጊቤ" የምትሰኘው በሆርሙዝ ሰርጥ ተዘግቶባት ለአራት ወራት በመቆየቷ ከፍተኛ ገቢ እንዲያጡ ማድረጉን ጠቁሟል።


መርከቧ ለአራት ወራት በመቆየቷ ከደረሰው የገቢ ማጣት ውጪ በመርከበኞች፣ በመርከቧ እና በጭነቱ ላይ ግን የደረሰ ጉዳት አለመኖሩን ተናግረዋል።


ጦርነቱ በፈጠረው የነዳጅ እጥረት ለጭነት ተሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆን መርከቦችን ለማንቀሳቀስም የነዳጅ እጥረት አጋጥሞ እንደነበር ተናግረዋል።


ተቋሙ በመጪው አምስት ዓመት እሰራዋለሁ ብሎ በቀረፀው ስትራቴጂ ተጨማሪ 16 መርከቦችን ለመግዛት ማቀዱንም አስረድቷል።


በእቅዱ መሰረት የመጀመሪያዎቹን ስድስት መርከቦች ግዢ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለመፈፀም አስቀድሞ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ "የግዢው ሂደት ከምን ደረሰ?" ስንል ዋና ስራ አስፈፃሚውን ኢንጂነር አብዱልበርን ጠይቀናል።


እሳቸውም በተለያዩ ምክንያቶች የግዢ ሂደቱ ባይጠናቀቅም ግዢውን የተመለከተው ዝርዝር ስራ ግን መጀመሩን ነግራናል።


በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ግዢውን ማሳካት ባይቻልም በ5 ዓመት ጊዜ ውስጥ ግን የ16ቱ መርከቦች ግዢ ይሳካል ብለው እንደሚያስቡ መልሰዋል።


ቴዎድሮስ ወርቁ

Recent Posts

See All
የምክክሩ ሂደት አሁን ላይ ከእያንዳንዱ ባለ 500 አባላት የስራ ቡድን የተመረጡ 30 አባላት ከስልታዊ ቡድኖች የቀረቡ የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦችን አቀናጅተው፣ 500 አባላት ላሏቸው 7 የስራ ቡድኖች ቅዳሜ ከሰዓት ማቅረብ ጀምረዋል፡፡

ነሐሴ 4 2018 የምክክሩ ሂደት አሁን ላይ ከእያንዳንዱ ባለ 500 አባላት የስራ ቡድን የተመረጡ 30 አባላት ከስልታዊ ቡድኖች የቀረቡ የአጀንዳ ምክረ ሀሳቦችን አቀናጅተው፣ 500 አባላት ላሏቸው 7 የስራ ቡድኖች ቅዳሜ ከሰዓት ማቅረብ ጀምረዋል፡፡ በአዲስ አበባ ላይ እየመከረ ያለው ቡድን ግን ጉዳዩ አከራካሪ ሆኖ በ

 
 
 
የአዲስ ኃይል ማስቀጠያ የዱቤ ክፍያ ወለድን ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ፡፡

ነሐሴ 4 2018 የአዲስ ኃይል ማስቀጠያ የዱቤ ክፍያ ወለድን ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ተናገረ፡፡ አገልግሎቱ አዲስ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስቀጠያ ክፍያን በዱቤ ለሚከፍሉ ደንበኞች ይጣል የነበረውን የወለድ ክፍያ ሙሉ በሙሉ ማንሳቱን የአገልግሎቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው አስረ

 
 
 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play
  • Facebook
  • X
  • Youtube
  • TikTok
  • Telegram
  • Whatsapp

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page