ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በደላሎች ተታልለው በደቡብ ምስራቅ እስያ ለአስገዳጅ የበየነ-መረብ ማጭበርበር ወንጀል እና ለእንግልት እየተዳረጉ ነው ተባለ።
- Jul 31
- 2 min read
ሐምሌ 23 2018
ከፍተኛ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ኢትዮጵያውያን በደላሎች ተታልለው በደቡብ ምስራቅ እስያ ለአስገዳጅ የበየነ-መረብ ማጭበርበር ወንጀል እና ለእንግልት እየተዳረጉ ነው ተባለ።
በቀን እስከ 18 ሰዓት ያለ እረፍት እንዲሰሩ ይገደዳሉ የተባሉት እኝህ ወጣቶች ለመሄድ ከ1 ሺህ እስከ 4 ሺህ 500 ብር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ተነግሯል።
የተሻለ ክፍያ የሚያስገኝ የስራ እድል አለ በሚል በደላሎችና በበይነ-መረብ (ኦን ላይን) በሚለቀቁ ሀሰተኛ ማስታወቂያዎች ተታልለው ከሀገር ከወጡ በኋላ በበይነ-መረብ በሚካሄዱ የተለያዩ የማጭበርበር ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ ይገደዳሉ።
በህገ-ወጥ መንገድ ከሀገር ወጥተው የተለያየ ጉዳት ደርሶባቸው የተመለሱትን በማገዝና ድጋፍ በማድረግ ላይ ትኩረቱን ያደረገው "ንጋት ግሎባል" የተሰኘው ድርጅት ባጠናው ጥናት፤ ተታልለው ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ከሚሄዱት መካከል 65 በመቶ ያህሉ የመጀመሪያ ዲግሪና ከዚያ በላይ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ናቸው ብሏል።
ጥናቱን ያቀረቡት የንጋት ግሎባል ኢኒሼቲቭ ድርጅት መስራችና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳንኤል መለሰ ፤ ተጎጂዎቹ ወደ ታይላንድ ፣ ማይናማር እና ካምቦዲያ የመሳሰሉ የደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት ለመሄድ ከ1 ሺህ እስከ 4 ሺህ 500 ዶላር መክፈል እንደሚጠበቅባቸው ነግረውናል።
ተጎጂዎቹ ወደ ተባሉት ሀገራት ሲደርሱም በበይነ-መረብ የማጭበርበር ስራ እንዲሰሩ ይገደዳሉ።
ለእያንዳንዳቸው በቀን የኮታ መጠን የሚሰጣቸው ሲሆን፣ የተባሉትን ማሳካት ካልቻሉ የመገረፍ ፣ በኤሌክትሪክ ሾክ የመመታት እና የከፋ አካላዊ ጉዳት እንደሚደርስባቸው አስረድተዋል።
ጥናቱ የቀረበው በሰው መነገድ ወንጀል መከላከል ላይ ትኩረቱን ባደረገው የፍትህ ሚኒስቴር ከአለም አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (IOM) ጋር በመተባበር ባሰናዳው የውይይት መድረክ ላይ ነው።
አቶ ዳንኤል አሁንም «የተሻለ ክፍያ የሚያስገኝ ስራ አለ» በሚል በርካታ የተማሩ ሰዎች ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት በመሄድ የሚሰቃዩና ተገደው የኦን ላይን ማጭበርበር ስራዎችን የሚሰሩ መኖራቸውን በማስታወስ፤ መንግስት ጠንካራ ዲፕሎማሲያዊ ስራ በመስራትና ከሲቪል ማህበራት ጋር በመነጋገር በችግር ላይ ያሉ ዜጎችን መመለስ አለበት ብለዋል።
በደላሎችና በሀሰተኛ የስራ ማስታወቂያዎች አምነው ወደ ደቡብ ምስራቅ እስያ ሀገራት በመሄድ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ 2,000 ገደማ ዜጎች በዚህ አመት መመለሳቸውም በመድረኩ ላይ ተጠቁሟል።
ተቋማት ተናበው በጋራ መስራት፣ በወንጀል ሰንሰለቱ የሚሳተፉ አካላት ተጠያቂ የሚሆኑበት እና የጉዳቱ ሰለባ የሆኑት የሚያገግሙበትና የሚደገፉበት መንገድ መሰራት እንዳለበት መድረኩ ተነስቷል።
በተመድ አማካኝነት በየአመቱ በመላው አለም የሚከበረው የአለም አቀፍ የፀረ-ሰው መነገድ ወንጀል ቀን በኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም በብሄራዊ ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ታስቦ መዋሉ ይታወሳል።
በየአመቱ እ.ኤ.አ ሐምሌ 30 በተለያዩ መሪ ቃሎች የሚከበረው ይህ ቀን ፤ ወንጀሉን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ሀገራት በህብረት ለመስራት ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩበት እንዲሁም ለተጎጂዎች መብትና ጥበቃ ለማድረግ ትኩረት ለመስጠት ቃል የሚገቡበት ነው።
ዕለቱ ዘንድሮ በአለም አቀፍ ደረጃ ለ13ኛ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ2ኛ ጊዜ ታስቦ ውሏል።
ገዛ ጌታሁን
_edited.jpg)


Comments