top of page

ሚያዝያ 17፣2016 - የቢዝነስ ስራዎች፤ የሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ እንዲፈፀሙ ያስፈልጋል ተብሏል

ማንኛውም የቢዝነስ ስራዎች፤ የሰብአዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ እንዲፈፀሙ ማድረግ ያስፈልጋል ተብሏል፡፡


ይህ የተባለው በፍትህ ሚኒስቴር፣ በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረትና በሌሎች አለም አቀፍ ተቋማት አጋዥነት በተሰናዳ ውይይት ላይ ነው፡፡


ውይይቱ ቢዝነስና የሰብአዊ መብትን ግንኙነት ላይ ያተኮረ ነው፡፡


በዚህ ላይ የውይይት መነሻ ሀሳብ ያቀረቡት የሰብአዊ መብት ባለሙያ ዶ/ር ወንድማገኝ ታደሰ የሰብአዊ መብቶች እና ቢዝነስ የማይነጣጠሉ አብሮ የሚሄዱ ናቸው ብለዋል፡፡

አንዳንዶች ቢዝነስና የሰብአዊ መብቶች ግንኙነት እንደሌላቸው አድርገው ይናገራሉ፤ ይህም ፍጹም የተሳሳተና ከግንዛቤ ማነስ የመጣ ነው ተብሏል፡፡


የሰብአዊ መብት የማክበር ባህላችን ወይም ልምዳችን በአደገ ቁጥር የቢዝነስ እንቅስቃሴው በዛው ልክ እየሰፉ ይሄዳሉ ተብሏል፡፡

ለዚህም መንግስት የሰብአዊ መብትና ቢዝነስ ያላቸውን ግንኙነት ተረድቶ ሁለቱ ታርቀው የሚሄዱበትን መላ መዘየድ አለበት ብለዋል፡፡


የኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት የፕሮግራም ሀላፊ በሬሳ አበራ በበኩላቸው መንግስት የሰብአዊ መብትን የማስከበር ግንዴታ እንዳለበት ጠቅሰው ያ ባለመሆኑ ግን የቢዝነስ ተቋማት ላይ በተለያዩ ምክንያት ጉዳት ሲከሰት አይተናል ብለዋል፡፡


በሀገሪቱ በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ግጭቶችም የቢዝነስ ተቋማትንም በተደጋጋሚ ዒላማ ያደረጉ ናቸው፤ ለዚህም በቅርቡ የተከሰቱ ግጭቶች ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡


በኢትዮጵያ አለመግባባቶችና ግጭቶች በተነሱ ቁጥር የቢዝነስ ተቋማት ለምን ቀዳሚ ተጎጂዎች እንደሆኑ ማረጋገጥ ይገባል ማለታቸውን ሰምተናል፡፡


የፍትህ ሚኒስቴር በበኩሉ ቢዝነስ እና የሰብአዊ መብቶች ተከባብረው የሚሄዱበትን መላ እየዘየድኩ ነው ብሏል፡፡


በፍትህ ሚኒስቴር የሰብአዊ መብቶች መርሃ ግብር ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ሀላፊ አቶ አወል ሱልጣን መንግስት የሰብአዊ መብቶችን ማክበር ፣ ማስከበርና እንዲለመዱ የማድረግ ግዴታ አለበት ብለዋል፡፡


እነዚህን ግዴታዎች ደግሞ መወጣት የሚቻለው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ሰፊ ውይይት አድርጎ ፖሊሲ ማውጣትና ማስፈፀም ሲቻል ነው ብለዋል፡፡


ያሬድ እንዳሻው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: @ShegerFMRadio102_1




bottom of page