top of page

ሚያዝያ 11፣2016 - በፈጠራ ስራዎች የመብት ባለቤትነት ክፍያ ዙሪያ በተናጠል ሲሰሩ የቆዩ 2 ማህበራት በጋራ ለመንቀሳቀስ ተስማሙ

በፈጠራ ስራዎች የመብት ባለቤትነት ክፍያ ዙሪያ በተናጠል ሲሰሩ የቆዩ ሁለት ማህበራት በጋራ ለመንቀሳቀስ ተስማሙ።


ማህበራቱ የየራሳቸውን የፈጠራ መብት የክፍያ ቀመር አዘጋጅተው ሲንቀሰቃሱ መቆየታቸውንም ተጠቅሷል።

የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ማህበራቱን ለማግባባት ወራት የፈጀ የማግባባት ስራ ሰርቷል ተብሏል።

ማህበራቱ፤ የኢትዮጵያ የቅጂና ተዛማች መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር እና የኢትዮጵያ የሙዚቃ፣ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር ናቸው፡፡


ህጋዊ ምዝገባ ያላቸው እና የጥበብ ባለሞያዎችን የሚወከሉት እነዚህ ማህበራት የስነ ፅሁፍ፣ የኪነ ጥበብ እና ተመሳሳይ የፈጠራ ስራዎች በመብት ባለቤቱ ስምምነት እና በክፍያ በቴሌቭዥን፣ በራዲዮ፣ በትራንስፖርት ድርጅቶች፣ በምሸት ክበቦች፣ በልዩ ልዩ መዝናኛ ቤቶች ወዘተ ለህዝብ አገልግሎት እንዲቀርቡ ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው ተነግሯል።


ከማህበራቱ አንደኛው በተለይ በሙዚቃ ስራዎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን የሚናገሩት የኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር፤ አቶ ወልዱ ይመስል ሌላኛው ደግሞ በሁሉም የጥበብ ውጤቶች ዙሪያ የሚሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።


ማህበራቱ የየራሳቸው የፈጠራ መብት ወይም ሮያሊቲ ክፍያ ቀመር አዘጋጅተው ሲንቀሰቃሱ መቆየተቸውን አቶ ወልዱ አስታውሰዋል።


ይህ በማህበራቱ መካከል የነበረ የተናጠል አካሄድ ከሚመለከታቸው አካላት ትብብር ማነስ እና ተያያዥ ምክንያቶች ጋር ተደማምሮ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ለዘጠኝ አመታት በሚፈለገው ደረጃ ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎ ቆይቷል ብለዋል፡፡

የተለያየ የሮያሊቲ ክፍያ በአንድ ሀገር መኖሩ ትክክል ስለማይሆን ማህበራቱ በጉዳዩ ላይ ወደ መግባባት እንዲመጡ ፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤታቸው ሲሰራ መቆየቱንም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።


አሁን በጋራ ሆነው የሮያሊቲ ክፍያ ቀመሩን እንዲያዘጋጁ ከስምምነት ደርሰናል ብለዋል።

የፈጠራ ስራዎች ባለቤት የሆኑ ሰዎች የሮያሊቲ ክፍያ ለማግኘት ከሁለት የአንደኛቸው ማህበር አባል መሆን ይኖርባቸዋል ሲሉ ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡


የተደሰረው ስምምነት ከፈጠራ ስራዎቻቸው ተጠቃሚ ለመሆን በተስፋ ሲጠብቁ ለቆዩ የፈጠራ ባለመብቶች ጥሩ ዜና እንደሆነም አቶ ወልዱ ተናግረዋል።


የሁለቱ ማህበራት ሃላፊዎችም ስምምነቱ የፈጠራ ስራ ባለመብቶች የሚገባቸውን ጥቅም እንዲያገኙ የሚረዳ ጥሩ ጅማሬ ነው ብለዋል።


ንጋቱ ረጋሣ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: @ShegerFMRadio102_1




bottom of page