top of page

ሚያዝያ 4፣2016 - በሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች የሚገኙ 842 ኢትዮጵያዊያን ዛሬ አዲስ አበባ መድረሳቸው ተሰምቷል

በተለያዩ የሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 842 ኢትዮጵያዊያን ዛሬ አዲስ አበባ መድረሳቸው ተሰምቷል።


በተለያዩ የሳውዲ አረቢያ እስር ቤቶች እና የማጎሪያ ቦታዎች የሚገኙ እና ከ70,000 የሚበልጡ ኢትዮጽያዊያንን ወደ ሀገር ለመመለስ በሚቻልበት ሁኔታ ዙሪያ ለመምከር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴታ ብርትኳን አያኖ ወደ ሪያድ መጓዛቸው ይታወሳል።


በተለያዩ ህገ ወጥ መንገዶች ሳውድ አረቢያ የሚደርሱ ኢትዮጵያዊያን ቁጥር በየወቅቱ እየጨመረ በመሄድ ላይ እንደሚገኝ የተነገረ ሲሆን አብዛኞቹ በወንጀል ተግባር ላይ ተገኝተዋል በሚል ምክንያት በሳውድ አረቢያ ታላላቅ እስር ቤቶች እና በተለያዩ የማጎሪያ ስፍራዎች እንደሚገኙ ተሰምቷል፡፡


የኢትዮጵያ መንግስት ከሳውድ አረቢያ ዜጎቹን ወደ ሀገር ለመመለስ አዲስ በጀመረው እና ሶስተኛ ዙር በሚል በጠራው ፕሮግራም ከሰባ ሺህ የሚበልጡ ዜጎችን የመመለስ እቅድ መያዙን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሳምንት በፊት ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።


መንግሥት ዜጎችን የመመለስ ፕሮግራሙን ተግባራዊ ለማድረግም ከአስራ ስድስት የሚበልጡ መንግስታዊ ተቋማትን የያዘ ግብረ ሀይል ማቋቋሙንም ተናግሯል።



በሳምንት በርካታ በረራዎችን በማድረግ ዜጎችን ወደ ሀገር ከመመለሱ እቅድ ጎን ለጎን ተመላሾችን የማቋቋም ስራውም እንደሚከናወን ሰምተናል።


በተለያየ ጊዜ ከሳውድ አረብያ ዜጎችን ወደ ሀገር የመመለሱ ተግባር የቀጠለ ቢሆንም በተመሳሳይ ተመላሾች ደጋግመው ወደ አረቡ አለም በህገ ወጥ እና በልዩ ልዩ መንገዶች እንደሚጓዙ ይሰማል።


የኢትዮጵያ መንግስት ባለፉት ሁለት እና ሶስት አመታት ከሳውድ አረብያ ብቻ ከ 300 ሺህ የማያንሱ ዜጎችን ወደ ሀገር መመለሱ የሚታወቅ ሲሆን የሳውድ አረቢያ መንግስት ህጋዊ የመኖሪያና የስራ ፈቃድ ያላቸውን ኢትዮጵያዊያንን ጭምር በጅምላ እያሰረ መሆኑ ይነገራል።


በተለያዩ ወንጀሎች ተጠርጥረው በሳውዲ አረቢያ ታላላቅ እስር ቤቶች እና ማጎሪያ ቦታዎች ተፈተው ወደ ሀገር ከሚመለሱት መካከል የአእምሮ ህመም የገጠማቸው እንዲሁም ህፃናትም እንደሚገኙበት እና አብዛኛዎቹ ተመላሾች ለረዥም አመታት በሳውድ አረቢያ በስራ ላይ የቆዩና ጥሪት ያፈሩ ቢሆኑም የሳውዲ መንግስት በጅምላ ወደ እስር ከከተታቸው በኋላ ወደ ሀገር ሲመለሱ ደጋግመን ተመላሾቹን እንዳየነው በእጃቸው ሰባራ ሳንቲም የሌላቸው መሆኑን ነው።


የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎችን ወደ ሀገር ለመመለስ የጀመረውን ሶስተኛ ዙር ዘመቻውን በቀጣዮቹ ቀናትም ያከናውናል መባሉን ሰምተናል።


የኔነህ ሲሳይ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: @ShegerFMRadio102_1




Comentarios


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page