ሚያዝያ 30 2017 - ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚሰጣቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ ማድረግ ላይ በአስፈጻሚ አካላት በኩል ችግር እንዳለ ተናገረ
- sheger1021fm
- 20 hours ago
- 2 min read
የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የሚሰጣቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ ማድረግ እና ተባባሪ መሆን ላይ አሁንም በመንግስት አስፈጻሚ አካላት በኩል ችግር እንዳለ ተናገረ።
ተቋሙ በዘንድሮው በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት በ32 መዝገቦች የተካተቱ 275 ሰራተኞች ወደ ስራ እንዲመለሱ እና የደረጃ ዕድገት እንዲያገኙ ማድረጉንም ጠቅሷል፡፡
የህዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም በመንግስት አስፈጻሚ አካላት እና በግል ድርጅቶች የሚፈጸሙ አስተዳደራዊ በደሎችን በመመመርመር ፤ የውሳኔ ሃሳብ የመስጠትና ተከታትሎ የማስፈጸም ሃላፊነት ተሰጥቶታል።

በ2017 በጀት አመት ዘጠኝ ወራትም ከዚሁ ጋር የተገናኙ ከ1 ሺህ 700 በላይ አቤቱታዎችን እንደተቀበለ አመልክቷል።
ከእነዚህ አቤቱታዎች ከመንግስት እና የልማት ድርጅቶች ሰራተኞች መብትና ጥቅም አከባበር ጋር የተገናኙት ከፍተኛውን ቁጥር እንደሚይዙ ተቋሙ ለሸገር በላከው መግለጫ ላይ ጠቅሷል፡፡
ከይዞታ አስተዳደር እና ከተለያዩ መንግስታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተገናኙ ቅሬታዎች ከፍ ባለ ቁጥር በዘጠኝ ወሩ እንደቀረቡለት አክሏል።
በዘጠኝ ወሩ የሰጣቸውን የውሳኔ ሃሳቦች ባልፈጸሙ አስፈጻሚ አካላት ላይ በ38 መዝገቦች ክስ መስርቶ 18ቱ ዕልባት እንዳገኙ ጠቅሶ በእስራትና ገንዘብ ተቀጥተዋል ብሏል።
ዕልባት እንዲያገኙ ከተደረጉ መዝገቦች መካከል በ32 መዝገቦች የተካተቱ 275 ሰራተኞች ወደ ስራ እንዲመለሱ ፤ የደረጃ ዕድገት እንዲያገኙ እና እስከ አስር ወር የሚደርስ እና ያልተከፈለ አንድ ሚሊየን አንድ መቶ ሃያ ሁለት ሺህ ብር ደመወዝ እንዲከፈላቸው ማድረጉንም በመግለጫው አስፍሯል።
በ12 መዝገቦች የተካተቱ 394 አቤቱታ አቅራቢዎች ከህግ አግባብ ውጪ የተከለከሏችውን የተለያዩ መንግስታዊ አገልግሎቶች እንዲያገኙ አድርጊያለሁም ብሏል።
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ለቡሳ ጎኖፋ ያለደረሰኝ ክፍያዎች የሚሰበሰቡበት መንገድ እንዲስተካከል እና
ቁጥጥር ባደረገባቸው የኢንዱስትሪ ፓርኮች ሴት ሰራተኞች እና አካል ጉዳተኞች ቅሬታ የሚያቀርቡበት አማራጭ መንገድ እንዲኖር የሚሉት ደግሞ ማስተካከያ ቢደረግባቸው በሚል ምክረ ሃሳብ ከሰጠባቸው ጉዳዮች መካከል እንደሆኑ ተቋሙ ጠቅሷል።
በአጠቃላይ ተቋሙ በበጀት ዓመቱ ዘጠኝ ወራት አስተዳደራዊ በደሎችን የመከላከል እና የተገኙትን ከማረም አንጻር ጥሩ ሊባሉ የሚችሉ ስራዎችን እንደሰራ በመግለጫው አመልክቷል፡፡
የሚሰጣቸውን የመፍትሄ ሃሳቦች ተግባራዊ ማድረግ እና ተባባሪ መሆን ላይ ግን አሁንም በአስፈጻሚ አካላት በኩል ችግር አለ ብሏል።
በደመወዝ እና ጥቅማ ጥቅም ማነስ ምክንያት የሚለቁ ባለሞያዎች እበና የበጀት እጥረትም የገጠሙኝ ሌሎች ችግሮች ናቸው ሲል ጠቅሷል።
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://shorturl.at/P4mpX
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://shorturl.at/21bFN