top of page

መጋቢት 12፣2016 - የገበያ ቅኝት - ስኳር ለማግኘት ለምን ብርቅ ሆነብን?

የምርት መጠናቸው ቀንሷል፣ ከገበያ ጠፍተዋል የተባሉ ምርቶች ላይ መንግስት ድጎማ ማድረግ ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል።


መንግስት ድጎማ አድርጎ ከሚያቀርባቸው መሰረታዊ ምርቶች መካከል ዘይት እና ስኳር ይገኙበታል።


ድጎማ ተደርጎበት በመንግስት ተቋማት በኩል ስለሚቀርበው ስኳር ባዛሬው የገበያ ውሎአችን ተመልክተነዋል።


የፍላጎቱን ያህል የማይመረተውን እና ከውጪም የሚገባው ስኳርን መንግስት በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል ለማህበረሰቡ እንዲቀርብ እያደረገ ቢሆንም ምርቱ ወሩን ጠብቆ አለመምጣቱ፣ ከሁለት ወራት በፊትም የ30 ብር ጭማሬ ማሳየቱ ህብረተሰቡን ፈትኖታል።


ስኳር አምራች ፋብሪካዎችን ማስፋት ምርቱ በበቂ ሁኔታ እንዲኖር ከምሰራቸው ስራዎች መካከል መሆኑን እወቁልኝ የሚለው መንግስት ፋብሪካዎቹን በተያዘላቸው ጊዜ መገንባት አልቻለም፣የተገነቡትም ቢሆን የታሰበውን ያህል ሊያመርቱ አልቻሉም፡፡


በመንግስት የሚቀርበው እና የሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል የሚሸጠው ስኳር በከተማዋ ያሉ ነጋዴዎች በሱቆቻቸው ላይ ሲሸጡ ይታያል። ለዚያውም በ120 እና 130 ብር።


በመንግስት ድጎማ ተደርጎበት የሚቀርበው ስኳር ነጋዴው እጅ ገብቶ 30 እና 40 ብር ጭማሪ ተደርጎበት በአደባባይ ሲሸጥ ይታያል፡፡


በሸማች ማህበራት ሱቆች ላይ ይስተዋል የነበረውን የስኳር ስረቆት እና ሌለውንም ችግር ለመፍታት ምርቱ ለህብረተሰቡ ካለምንም እንግልት እንዲደስር እና ህገወጥነት ለማስቀረት ይረዳል የተባለ የቤት ለቤት ግብይት አመቻችቼ እየሰራሁ ነው ብሏል የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ።


ይሄው ግብይትም ከተጀመረ ከሁለት አመት በላይ ያስቆጠረ ቢሆንም አሁንም በሙከራ ደረጃ ላይ እንዳለ ሰምተናል።


ግብይቱም ህብረተሰቡ ወደ ሸማች ማህበራት መሄድ ሳይጠበቅበት ስኳሩ በየቤቱ እንዲደርስ በዘመናዊ መንገድ እየሰራ ነው የተባለው የማኪባ ጠቅላላ ንግድ ነው።


አዲስ አበባ ከተማ በየወሩ የሚያስፈልጋት የስኳር ፍጆታ 120 ሺህ ኩንታል ቢሆንም፣ ከተማዋ ከኢትዮጵያ ከስኳር ኮርፖሬሽን እያገኘች ያለችው የስኳር ግን በየወሩ ተለዋዋጭ ነው ተብሏል፡፡


ለከተማዋ ከኢትዮጵያ ከስኳር ኮርፖሬሽን በጥር ወር የፍላጎቱን አንድ አራተኛ ወይንም 30 ሺህ ኩንታል፣ በየካቲት ወር ደግሞ የፍላጎቱን ግማሽ ወይንም 60 ሺህ ኩንታል ብቻ መቅረቡን ከንግድ ቢሮ ሰምተናል፡፡


ስኳርን ለማግኘት ለምን ብርቅ ሆነብን? በሸማች ማህበራት በኩል ለተጠቃሚው የሚቀርበው ስኳር ለምን ዋጋው ጨመረ?


ሸገር ይሄንን እና ሌሎች ጥያቄዎችን ይዞ ወደ አዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ሄዷል።


ፋሲካ ሙሉወርቅ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2024 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page