top of page

ግንቦት 13፣2016 - ታሪክን የኋሊት - መንግስቱ ሀይለማርያም፣ ሸሽተው ከሀገር የወጡት ከ33 ዓመታት በፊት በዛሬው ቀን ነበር

ኢትዮጵያን ለ17 አመታት እንደፈቀዱና እንደፈለጉ ሲገዙና ሲነዱ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ሀይለማርያም፣ የተቃዋሚ የጦር ሀይል ወደ አዲስ አበባ ሲቃረብ፣ ሸሽተው ከሀገር የወጡት ከዛሬ 33 ዓመታት በፊት ልክ በዛሬው ቀን ነበር፡፡


እለቱ ማክሰኞ ነበር፡፡


ከስድስት ሰዓቱ የኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ የዜና እወጃ፣ በሀገሪቱ የነበረውን ደም ማፈሰስ ለማስቆም ሲባል ፕሬዚዳንት መንግስቱ ከሀገር እንዲወጡ መደረጉ ተነገረ፡፡


በማግስቱ ግን ለማንም ሳያሳውቁ ሸሸተው፣ መሄዳቸውን የመንግስት ምክር ቤት ተናገረ፡፡


ምክትል ፕሬዘዳንት የነበሩት ፣ ሌፍተናንት ጀነራል ተስፋዬ ገ/ኪዳንም የሀገሪቱ ፕሬዘዳንት ሆነው የተሰየሙት በዛሬው ቀን ነበር፡፡


ሌተናል ኮሎኔል መንግስቱ፣ የተቀሰቀሰውን የየካቲት 66 ህዝባዊ አመፅ፣ በአዝጋሚ መፈንቅለ መንግስት እጁ ያደረገው ወታደራዊ ጁንታ (ደርግ) ሊቀመንበር ነበሩ፡፡


የኢሠፓ ዋና ፀሀፊ፣ የጦር ሀይሎች ጠቅላይ አዛዥ፣ የኢሕዲሪ ፕሬዝዳንት በሚል በተደራረቡ ሹመቶች ራሳቸውን ሾመው ኖሩ፡፡ ይሁንና አስተዳደራቸው ገና ከጅምሩ ግድያን መፍትሔ በማድረጉ፣ ተቃዋሚያቸው በዛ፡፡


መንግስታቸውን በመቃወም ተቃዋሚ ሀይሎች ጠመንጃ አንስተው ጥቃት ጀምረው ድል አገኙ፡፡


በሺ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ ሶስት ዓ.ም አጋማሽ ላይ፣ ተቃዋሚው የኢህአዴግ ሰራዊትም ወደ አዲስ አበባ በአሸናፊነት ገሰገሰ፡፡


ተቃዋሚዩቻቸው እንደተጠጓቸው ያዩት ኮሎኔል መንግስቱ፣ እምንሞተውም እምንኖረውም፤ እዚሁ ሀገራችን ላይ ነው የሚለውን ንግግራቸውን ሰርዘው ግንባሬ እስኪበተን ድረስ ትግሌን እቀጥላለሁ፤ ይሉ የነበሩትን አጥፈው ፤ ቤተሰባቸውን ይዘው ወደ ዚምባብዌ ሸሹ፡፡


ከመሸሻቸው አንድ ቀን በፊት የዚምባብዌ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አዲስ አበባ ድረስ መጥተው ሲያነጋግሩዋቸው ታይተዋል፡፡

ወደ ኬንያ ለመሄዱ አውሮፕላን እንዲዘጋጅላቸው ያረጉት ወደ ብላቴና ማስልጠኛ ገብተው ወታደራዊ ስልጠና በማድረግ ላይ የነበሩትን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎችን እጐበኛለው በሚል ሰበብ ነበር፡፡


ጉዞዋቸው ከረዳታቸው ሻምበል መንግስቱ ገመቹና የደህንነት ሚኒስትሩ ተስፋዬ ወልደስለሴ ብቻ ነበሩ፡፡


ከብላቴና ወደ አስመራ ከዚያም ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ በሚል ሰበብ፣ አውሮፕላኗ ነዳጅ እንድትሞላ አዘዙ፡፡ ረፋድ ላይ በረራቸውን ጀመሩ፡፡


በአየር ላይ እንዳሉ አውሮፕላኑ ወደ ብላቴና ሳይሆን ናይሮቢ እንዲበር አስገደዱት፡፡


አብራሪው፣ ወደ ኬንያ ለመብረር፣ ካርታ እንደሌለው እና መብረር እንደማይችል አሳወቀ፡፡ መንግስቱ ግን በግድ ትሄዳታለህ ብለው አስገደዱት፡፡


በዚህም፣ የሀገር መሪ ሆነው፣ አውሮፕላን ለመጥለፍ፣ የመጀመሪያው መሪ ናቸው ተብለዋል፡፡


ናይሮቢ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ፣ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ሁለተኛ ፀሀፊ ተቀበሏቸው በዚያው የስደተኝነት ኑሩዋቸውን ወደሚገፉበት፣ ወደ ሀረሬ ከአምስት አጃቢዎቻቸው ጋር ሄዱ፡፡


ኮሎኔል መንግስቱ፣ በስልጣን ዘመናቸው ሀገሪቱን እርስ በርስ በሚያፋጅ ፖሊሲ፣ ለስልጣናቸው ቅድሚያ ሰጥተው፣ ሀገሪቱን የስቃይ እና የፍዳ መፈልፊያ አደረጓት፡፡ ታይቶ በማይታወቅ ውርደትም ከተቷት የሚሏቸው አሉ፡፡


አንዳንዶች ደግሞ ማህበራዊ ለውጥ ለማምጣት የመሬት አዋጅን የመሳሰሉ ለማስፈፀም አስተዋፅኦ አድርገዋል ይሏቸዋል፡፡


ስለ እርሳቸው የፀፉ ሁሉም ግን በስልጣን ጥማት የታወሩ መሆናቸው እና በዚህም ከመጡባቸው ማንኛውንም አደጋ ለማድረስ የማይተኙ አምባገነን መሆናቸውን ይስማማሉ፡፡


በዘመነ መንግስታቸው፣ እርስ በርስ በተደረገ ፍጀት እና ጦርነት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጐች ደማቸው በየጎዳናው ፈሷል፡፡


የዲሞክራሲና የሰብአዊ መብቶች የሚባሉ ነገሮች ፣ እንኳን በውን በሕልም እማይታስብበት፣ ሀገር ማለት ርሳቸውና እና ፓርቲያቸው ብቻ እንዲሆን የሚያስችል አሰራር የሚከተሉ ነበሩ ፣ይሏቸዋል፡፡


መጨረሻቸው ግን፣ የፎከሩበትን ሁሉ ሳይፈፅሙ፣ ደጋፊዎቻቸው የሰጧቸውን “ቆራጡ” የሚል ስያሜ ተግባራዊ ሳያደርጉ፣ ሁሉንም ጣጥለው ፈረጠጡ፡፡


ኮሎኔል መንግስቱ አሁንም በስደት በሀራሬ እንደሚኖሩ ይነገራል፡፡


ሌፍተናል ጀነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን በ8 ቀናት የስልጣን ቆይታቸው፣ በአዲስ አበባ እልቂት እንዳይፈፀም፣ ሰራዊቱ ጠመንጃውን እንዲያስቀምጥ መግለጫ ከመስጠት ያለፈ ስራ ሊሰሩ አልበቁም፡፡


ኮሎኔል መንግስቱ፣ በሸሹ በ8ተኛው ቀን፣ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ተቆጣጠረ፡፡


እሸቴ አሰፋ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw


Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio


Website: https://www.shegerfm.com/


Comments


bottom of page