top of page

የካቲት 20፣2016 - ምርጫ ቦርድ ለ‘’ሳልሳይ ወያነ ትግራይ’’ ፓርቲ የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሰጠ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ‘’ሳልሳይ ወያነ ትግራይ’’ የክልላዊ ፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት ሰጠ።


ቦርዱ ለፓርቲው የምዝገባና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የካቲት 18 ቀን 2016 ዓ ም መሰጠቱን ዛሬ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ይፋ አድርጓል።


‘ሳልሳይ ወያነ ትግራይ’ ከሶስት ዓመት በፊት በአመጽ ተግባር ተሳትፈዋል በሚል ማብራሪያ እንዲያቀርቡ በቦርዱ ከታዘዙ ፓርቲዎች አንዱ እንደነበር ይታወሳል።


ባይቶና እና ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሕገ ወጥ በተባለው ምርጫ ላይ መሳተፋቸውንና አመራሮቻቸውም በአመጽ ተግባር ላይ መሰማራታቸውን የሚያመለክት መረጃ በማግኘቴ ማብራሪያውን እንዲያቀርቡ አዝዣለሁ ብሏል ቦርዱ በጊዜው።



ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲም እንዲሁ በትግራይ ክልል በተካሄደው የተናጠል ምርጫ ላይ መሳተፉን ተከትሎ ማብራሪያ እንዲያቀርብ መታዘዙ ይታወሳል።


የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር የቆየውን የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)ን ሕጋዊ ሰውነት መሰረዙን ቦርዱ የዛሬ ሶስት ዓመት ግድም አሳውቆ ነበር::


ቦርዱ በጊዜው ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ህወሓት በአመጽ ተግባር ላይ መሰማራቱን በተመለከተ ለማጣራት በፓርቲው የተሰጡ መግለጫዎችንና "በይፋ የሚታወቁ ጥሬ ሃቆችን በማቅረብ ፓርቲው ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሣተፉን" በማረጋገጡ እንደሆነ አመላክቶ ነበር።


ከሁለት ሳምንት በፊት የፌዴራል መንግሥትና የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት አፈጻጸም በአዲስ አበባ ተገናኝተው በገመገሙበት ወቅት ይኸው ጉዳይ እንደተነሳ ተነግሯል።


የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ከውይይቱ በኋላ በመቀሌ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይህንኑ አረጋግጠዋል።


የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዲመለስ ማድረግን በተመለከተ በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መሪነት በተካሄደው ግምገማ ላይ ከመግባባት ደርሰናል ብለዋል።


የሕወሓት ሕጋዊ ሰውነት እንዳይመለስ እንቅፋት የሆኑ የሕግ ጉዳዮች በፍጥነት መፍትሄ እንዲሰጣቸው ከስምምነት መደረሱንም ተናግረዋል።


በዚህም ሕወሓት በምርጫ ቦርድ እንዲመዘገብና ዕውቅና እንዲያገኝ ተስማምተናል ብለዋል።


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለ‘ሳልሳይ ወያነ ትግራይ’ የክልላዊ ፖለቲካ ፓርቲ የምዝገባና የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የሰጠበት ውሳኔ ከዚህ ስምምነት ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ግን የታወቀ ነገር የለም።


ቦርዱም የሰጠው ዝርዝር መረጃ የለም።



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2024 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page