top of page

ታሪክን የኋሊት - ሚያዝያ 30 2017 - ሶቪየት ህብረት፣ በአሜሪካ በሚዘጋጀው ኦሎምፒክ እንደማትሳተፍ ያስታወቀችበት ቀን ነበር

  • sheger1021fm
  • 2 days ago
  • 1 min read

በርካታ ቁጥር ያላቸውን አትሌቶች የምታሰልፈው ሶቪየት ህብረት ፣ በአሜሪካ በሚዘጋጀው ኦሎምፒክ እንደማትሳተፍ ያስታወቀችው በ1976 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡


ሎስአንጀለስ ላይ በተዘጋጀው ኦሎምፒክ ፣ ሶቪየት ህብረት አልወዳደርም፣ ያለችው አትሌቶቼ የተቃውሞና ምናልባትም የአካል ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል፤ የሚል ምክንያት ሰጥታ ነው፡፡


ነገር ግን የሶቪየት ህብረት ፣ በአሜሪካ የሚዘጋጀውን ኦሎምፒክ ፣ ለመሳተፍ ያልፈለገችው፣ ከአራት አመታት በፊት ሞስኮ ተደርጎ በነበረው ኦሎምፒክ አሜሪካ ባለመሳተፏ ነበር፡፡


አሜሪካና አጋሮቿ በሞስኮው ኦሎምፒክ አንሳተፍም ያሉት ፣ ሶቪየት ህብረት በአፍጋኒስታኒን ወራለች ብላ ነበር፡፡


በጊዜው ፣ ሶቪየት ህብረት ፣ በእነ አሜሪካ የሚደገፉትን አማፅያን እንቅስቃሴ ለመግታት ፣ የአፍጋኒስታን መንግስት ባቀረበችላት ጥያቄ መሰረት ወታደሮቿን ወደ ካቡል አሰማርታ ነበር፡፡


የሎስ አንጀለሱ ኦሎምፒክ ከጀመሩ ወራቶች በፊት ፣ “ከዝግጅቱ የመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ፣ የአሜሪካ መንግስት ኦሎምፒክን ለፖለቲካ ግቡ ማስፈፀሚያ እያደረገው ነው፡፡ ትምክህተኛና ፀረ ሶቪየት አስተያየቶችን ሲያስተላልፍ ቆይቷል..” ሲል የሶቪየት ህብረት መግለጫ አወጣ፡፡


በሶቪየት አትሌቶችም ላይ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉንና ሹማንቶቹ እቅዱን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ ናቸው ብላ እንደማታምን ጠቅሳ አሜሪካን ከሰሰች፡፡

የፕሬዘዳንት ሬጋን መንግስት ፣ የሶቪየት ህብረት ውሳኔ ፣ ማስረጃ የማይቀርበት ፖለቲካው ውሳኔ ነው ሲል ክሱን አጣጣለው፡፡


የሶቪየት ህብረትን ውሳኔ ተከትሎ ኢትዮጵያን ጨምሮ 15 የሶሻሊስት ሃገሮች ሌሎች አራት ሀገሮች በራሳቸው ምክንያት ፣ በጠቅላላ 19 ሃገሮች በሎስአንጀለሱ ኦሎምፒክ እንደማይሳተፉ አስታወቁ፡፡


ኢትዮጵያና ብዙዎች ሃገሮች ላለመሳተፍ የሰጡት ምክንያት ለአትሌቶቻችን ደህንነት እንሰጋለን የሚል ሲሆን ፣ ኪዩባ ግን የማልሳተፈው ለሶቪየት ህብረት ያለኝን ወዳጅነት ለመግለፅ ብቻ ነው አለች፡፡


በጊዜው በቀዝቃዛው ጦርነት የምዕራብና የምስራቁ አለም ከፍተኛ ፍንጫና ውጥረት ላይ የገቡበት ጊዜ ነበር፡፡


የሎስአንጀለሱ ኦሎምፒክ 140 ሃገሮች ቢሳተፉበትም በዚያ በፊት የኦሎምፒክ አሸናፊ የነበሩ በርካታ አትሌቶች ያልተሳተፉበት በመሆኑ ፣ አሜሪካ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ 83 የወርቅ ሜዳሊያ ሰበሰበች፡፡


ሶቪየት ህብረት በሎስአንጀለሱ ኦሎምፒክ እንደማትሳተፍ ካስታወቀች ፣ 41 ዓመት ሆነ፡፡


እሸቴ አሰፋ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…






Comentários


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page