ላለፉት 6 ዓመታት በጉምሩክ ተይዘውብኝ የነበሩት ኮምፒውተሮች ተለቀውልኛል ሲል ራዕይ የህፃናት መርጃ ድርጅት ተናገረ፡፡
- sheger1021fm
- 2 hours ago
- 2 min read
ህዳር 10 2018
ላለፉት 6 ዓመታት በጉምሩክ ተይዘውብኝ የነበሩት ኮምፒውተሮች ተለቀውልኛል ሲል ራዕይ የህፃናት መርጃ ድርጅት ተናገረ፡፡
ይህ የሆነው ጉዳዩን ወደ ሚዲያ ካመጣሁት በኋላ ነውም ብሏል፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የአዕምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ህፃናት ለማሰልጠን ሊውል የነበረና በልገሳ ከውጭ ሃገር ያስገባሁት ኮምፒውተር በጉምሩክ ተይዞ 6 ዓመት ሆነው ሲል የህፃናት መርጃ ድርጅቱ ተናግሮ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ከድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ ወ/ሮ ሰሎሜ ኩምሳ እንደሰማነው መረጃው በሚዲያ በተሰራጨ ማግስት ከድርጅቱ የክብር አምባሳደር አትሌት መሰረት ደፋር ጋር በመሆን ድርጅቱ ለጉምሩክ ኮሚሽን ኮምፒውተሮቹ እንዲመለሱለት ያቀረበው ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አግኝቶ፤ 107 ኮምፒውተሮች፣ እንደ ኪቦርድ፣ ጊታር፣ ድራም ያሉ የሙዚቃ መሳሪያዎችን፣ የልጆች መጫወቻዎችንም ጭምር ተከማችቶ ከነበረበት ተረክበናል ብለዋል፡፡

ወ/ሮ ሰሎሜ እቃዎቹ ለ6 ዓመታት በጉምሩክ ተይዘው የመቆየታቸውን ምክንያት ወደ ሃገር ቤት ሲገቡ የተጫኑት ከሌሎች የህክምና እቃዎችና የትምህርት መሳሪያዎች ጋር ተቀላቅለው ስለነበር ኮሚሽኑ እነርሱን ለመለየት በመቸገሩ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡
እቃዎቹን ያገኘነው ደህንነታቸው እንደተጠበቀ ነው ነገር ግን በመቀመጥ ብዛት ያለመስራት ሊኖር ስለሚችል፤ መስራታቸውን እያረጋገጥን ለየትምህርት ቤቱ ማከፋፈል ጀምረናል የሚሉት የድርጅቱ የኢትዮጵያ ተጠሪ ወ/ሮ ሰሎሜ፤ የኮምፒውተር ላቦራቶሪ አዘጋጅተውና መምህራንንም አሰልጥነው ለዓመታት የኮምፒውተሩን መምጣት ሲጠባበቁ ከነበሩ ትምህርት ቤቶች መካከል አንዱ ለሆነው ትንቢተ ኤርሚያስ ቅድመ አንደኛና የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ለጊዜው 10 ኮምፒውተሮችን ሰጥተናል፤ በዚህ መንገድ በአዲስ አበባ ላሉና ድርጅቱ የሚደግፋቸው የልዩ ፍላጎት ተማሪዎች ላሉበት 4 የመንግስት ትምህርት ቤቶች እናከፋፍላለንም ብለውናል፡፡
ከዚህ በኋም ከውጭ የምናስመጣቸው እቃዎች መሰል እክል እንዳይገጥማቸው ለማድረግ በሂደቱ መስፈርቶችን አሟልተን ከቀረብን የሲቪል ማህበረሰብ ኤጀንሲም እንደሚገፈን ቃል ገብቶልናል፤ እቃውን በማስመለሱ ሂደት ለተባበሯቸውንና ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ ድምፅ የሆኗቸውን በሙሉ አመስግነዋል።
ላለፉት 9 ዓመታት ራዕይ የህጻናት መርጃ ድርጅት የእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው፣ኦቲዝምና ሌሎችም ችግሮች ያሉባቸው ህፃናት ትምህርት እንዲያገኙና ክህሎታቸውን እንዲያዳብሩ እያገዘ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ድርጅቱ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ባሳለፍነው ህዳር 4 ቀን 2018 ዓ.ም በአዳማ ከተማ በሚገኘው ሌተና ኮሎኔል ደጀኔ ስሜ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ፣ የአዕምሮ እድገት ውስንነት ላለባቸው ህፃናት የእንክብካቤ ማዕከል ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ ማስቀመጡንም ከሃላፊዋ ሰምተናል።
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ….
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s








