top of page

ፋሽስት ኢጣሊያ ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚገኙ 300 መነኮሳትና ዲያቆናት በመደዳ በጥይት ያስደበደባቸው፣ በ1929 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡

  • May 20
  • 2 min read

ፋሽስት ኢጣሊያ ፣ በደብረ ሊባኖስ ገዳም የሚገኙ 300 መነኮሳትና ዲያቆናት በመደዳ በጥይት ያስደበደባቸው፣ በ1929 ዓ.ም በዛሬው ቀን ነበር፡፡


መነኮሳቱና ዲያቆናቱ እንዲገደሉ ትዕዛዝ የሰጠው ጀኔራል ሮዶልፎ ግራዚያኒ ነበር፡፡


ጀኔራል ግራዚያኒ የኢጣሊያ የምስራቅ ዕዝ አዛዥና በኋላም የኢትዮጵያ የቅኝ ግዛት ገዥ በነበረበት ጊዜ ሁሉ፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና መነኮሳት ላይ የተለየ ጥላቻ ነበረው፡፡


የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት፣ ኢትዮጵያ እንዳትገዛልን የሚያወግዙ፣ ስለነፃነት የሚሰብኩ፣ አርበኞችን የሚደግፉ ናቸው ፤ የሚል እምነት ስለነበረው ቤተ ክርስቲያኗን ለመበተን ይመኝ ነበር፡፡


የካቲት 12፣ አብርሃም ደቦጭ በቦምብ ካቆሰለው በኋላ ፣ሚስቱን ደብረ ሊባኖስ ገዳም መደበቁን ሰማ፡፡


ይኽም በካህናት መነኮሳት ላይ ያለውን ጥላቻ አጠናከረለት፡፡


ለሸዋ ጦር አዛዠ ፣ለጀኔራል ማልቲ፣ አደጋ የጣሉብኝ ሰዎች በግዛትህ ሲዘዋወሩ ባለመያዝህ ሀላፊነት ትወስዳለህ ብሎ ተቆጣው፡፡


በቴሌግራም ቁጥር 26320 በደብረ ሊባኖስ መነኮሳት ላይ የግድያ ርምጃ እንዲወሰድ ከገዳሙ አለቃ ጀምሮ ያለምንም ምርጫ መነኮሳቱ ዲያቆናት እንዲረሸኑ ትዕዛዝ አስተላለፈለት፡፡


ጀኔራል ማልቲ፣ በርካታ ቁጥር ባላቸው ወታደሮች ታጅቦ ግንቦት 12 ደብረ ሊባኖስ ደረሰ፡፡


እለቱ የአቡነ ተክለሃይማኖት በዓል የሚከበርበት ቀን በመሆኑ በርካታ ሰው ተሰብስቧል፡፡


የተራራውን ዙሪያ በወታደር አስከበበው፡፡


ወደ ገዳሙ ሲደርስ ፣ ሊቀበሉት የተሰለፉትን የካህናት “እናንተ ቁጥራችሁ ትንሽ ነው፡፡ ሌሎቹ ለምን አልተቀበሉኝም” ብሎ ተቆጣ፡፡


የተቀበሉትን በቅጥር ግቢው እንዲቆዩ አዞ ፣ሌሎቹን መምህራንና መነኮሳት ታድነው እንዲያዙ አዘዘ፡፡


300 የሚሆኑ ሞታቸውን የሚጠብቁ አዛውንትና መነኮሳት፣ ዲያቆናትና የንግስ በዓል ለማክበር የሄደውን ሕዝብ እያስገደደ በመኪና ጫናቸው፡፡


ከገዳሙ ወጣ ብሎ በሚገኘው ሽንኩርት ከተባለው ቀበሌ ሲደርሱ፣ ከመኪና አስወርዶ 300 የሚሆኑትን በጥይት አስደበደባቸው፡፡


ሌሎቹ በዓል ለማክበር ደብረ ሊባኖስ የተገኙትንና ዲያቆናትን ወደ ደብረ ብርሃን ትሄዳላችሁ ብሎ አሳፈራቸው፡፡


በመንገድም ላይ ሲደርሱ 129 የሚሆኑትን ዲያቆናት ገደላቸው፡፡


ጀኔራል ማልቲ ይኽንም ለአለቃው ለግራዚያኒ እለቱን ሪፖርት አደረገ፡፡


ከአሰቃቂው ግድያ በኋላ ወታደሮች ገዳሙን ዘረፉት፡፡


የደብረ ሊባኖስ ገዳም ፣ መኳንንትና ዝና ያላቸው ኢትዮጵያዊውያን የተቀበሩበት ገዳም ስለሆነ አብሩዋቸው ወርቅ ተቀብሮ ይሆናል እያሉ ቀብራቸውን እየከፈቱ አዩ፡፡


ከሁሉም ብልጫ ያለው ንብረትና መፃህፍት የሚገኙበትን የደብረሊባኖስ ገዳም ጣሊያኖች ያገኙትን ሁሉ መዝብረው ወናውን አስቀሩት፡፡


ገዳሙ ለአገልግሎት ዝግ ሆኖ፣ ቁልፉ ለአካባቢው የኢጣሊያ ሹም መሰጠቱን ግራዚያኒ በቴግራም ለሮም አሳውቋል፡፡

በግራዚያኒ ትዕዛዝ 429 የደብረ ሊባኖስ ገዳም መነኮሳት ፣ ካህናት መምህራንና ሲቪሎች ከተገደሉ ዛሬ 88 ዓመት ሆነ፡፡


እሸቴ አሰፋ


ግንቦት 12/2018


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2026 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page