top of page

ነሐሴ 24፣2015 - ፋርማ አፍሪካ እና ሲዳ በኢትዮጵያ የብዝኃህይወት ጥበቃን የሚያበረታ ፕሮግራም ይፋ ማድረጋቸው ተናገሩ


ዋና መቀመጫውን በእንግሊዝ ያደረገው ፋርማ አፍሪካ እና የስዊድኑ አለም አቀፍ የእድገት ትብብር ኤጀንሲ /ሲዳ/ በኢትዮጵያ የብዝኃህይወት ጥበቃን የሚያበረታ ፕሮግራም ይፋ ማድረጋቸው ተናገሩ፡፡


ለፕሮጀክቱም 11.5 ሚሊዮን ዶላር ወይንም 664 ሚሊዮን ብር ግድም መስጠታቸው ታውቋል፡፡


ተፈጥሮን ማዕከል አድርጎ ይሰራል የተባለው የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ፕሮጀክት ለ4 ዓመታት የሚተገበር መሆኑንን ፋርማ አፍሪካ ለሸገር በላከው መግለጫ ላይ ጠቅሷል፡፡


በፕሮግራሙ የደን እና የብዝሃ ሕይወት ጥበቃ፣ ማህበረሰቡ በአየር ጠባይ ለውጥ ተጎጂ እንዳይሆን የአቅም ግንባታ ስራዎችን መስራት እንደሚያካትት ተነግሯል፡፡


በ11.5 ሚሊዮን ዶላር የሚሰራው የብዝሃ ህይወት ጥበቃ ስራ በዋቢ ሸበሌ፣ ገናሌ ዳዋ፣ ኦሞ ጊቤ እና ባሮ አኮቦ እና ስምጥ ሸለቆ እንዲሁም አዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎችን ላይ እንደሚሰራ ተጠቅሷል፡፡


በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ገበሬዎች በርካታ ችግሮች ይገጥሟቸዋል ያለው መግለጫው በተለይ የግብርና ግብአት እጥረት፣ ዘላቂነት ያለው የመሬት አስተዳደር ከሚያጋጥሙት ችግሮች መካከል ናቸው፡፡


በዚህም የተነሳ የአፈር ለምነት፣ የግብርና ምርታማነት እንደሚቀንስ ይህ ደግሞ የምግብ ደህንነት ችግር ላይ እንደሚጥል ድርጅቱ አስታውሷል፡፡


ይህንን ችግር ለመቀነስ ፕሮጀክቱ ማስፈለጉ የተነገረ ሲሆን የተፈጥሮ ሀብትን፣ ብዝሃ ህይወትን እንዲሁም ስነ ምህዳርን ለመጠበቅ የሚያግዙ ስራዎች ይሰራሉ ተብሏል፡፡


በአራት አመቱ ፕሮግራም 87 ሺህ አባወራዎችን ይጠቀማሉ መባሉን ሰምተናል፡፡


አፋር፣ አማራ፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ፣ ሶማሊ፣ ደቡብ፣ ደቡብ ምዕራብ ክልሎች እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፕሮጀክቱ የሚተገበርባቸው አካባቢዎች መሆናቸው ተነግሯል፡፡


ንጋቱ ሙሉ

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

bottom of page