ጳጉሜ 5፣2016 - የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ለአዲስ ዓመት በዓል የእንሰሳት እርድ ለመከወን ተዘጋጅቻለሁ አለ
- sheger1021fm
- Sep 10, 2024
- 1 min read
የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ከፊታችን ለሚከበረው የአዲስ ዓመት በዓል፤ 5,000 ያህል የእንሰሳት እርድ ለመከወን ተዘጋጅቻለሁ አለ።
በቀን የ3,500 እንሰሳትን እርድ የመከወን አቅም አለኝ የሚለው ድርጅቱ ይሁንና ከማህበረሰቡ የሚቀርብልኝ የእርድ እንሰሳ ቁጥር ጥቂት በመሆኑ ከአቅሜ በታች ለመስራት ተገድጃለሁ ሲል በተደጋጋሚ ይደመጣል።
በዓሉን ምክንያት በማድረግ የማረድ አቅሙን በቀን ወደ 5 ሺህ ከፍ ማድረጉና ከዚህም ውስጥ 3,000 በሬ 2,000 በግና ፍየል ማረድ እንደሚችል ዛሬ በሰጠው መግለጫ ተናግሯል።

መግለጫውን የሰጡት የቄራዎች ድርጅት የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አታክልቲ ገብረ ሚካኤል ለበዓሉ ጤንነቱ የተጠበቀ እርድ እንዲከወንላቸው የሚፈልጉ ሁሉ በግና ፍየል በ165 ብር በሬ በ1,473 ብር እናርዳለን ብለዋል።
የእርድ አገልግሎቱ ቄራ አካባቢ በሚገኘው ቅጥር ግቢውና አቃቂ ቃሊቲ አካባቢ ባለው ቅርንጫፉ የሚከወን ነው ብሏል።
ይህንን ስራ ለመስራት 45 የስጋ ማጓጓዣ ተሸከርካሪዎች፣ ከ40 በላይ የእንሰሳት ህክምና ባለሙያዎች እና ከመደበኛ ውጪ ተጨማሪ ሰራተኞች ዝግጁ ሆነው እየተጠባበቁ መሆኑም ተነስቷል፡፡
ለእርድ ወደ ድርጅቱ የሚመጡ እንሰሳት በሙሉ ከእርድ በፊት ምርመራ ተደርጎላቸው ጤንነታቸው ይረጋገጣል፡፡
የተሟላ ጤንነት ከሌላቸው ለእርድ አይቀርቡም ተብሏል፡፡
ሲታረዱም እንደየ እምነት ተቋሙ በክርስትና እና በእስልምና እምነት አባቶች ተባርኮ እንደሆነ ሃላፊው አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል ድርጅቱ ባዘጋጃቸው የስጋ መሸጫ ሱቆቹ የበግና የፍየል ስጋ በኪሎ 610 ብር የበሬ ስጋ 700 እንደሚሸጥ ጠቁመዋል፡፡
በየስፍራው በሚከወነው ህገወጥ እርድ ምክንያት በየዓመቱ ማግኘት የነበረበትን ከ1.5 ቢሊዮን በላይ ገቢ እንደሚያጣም አቶ አታክልቲ ሲናገሩ ሰምተናል።
ህገ ወጥ እርድን ለመከላከል ከደምብ ማስከበር ባለስልጣን ጋር እየሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ቄራዎች ድርጅት ተናግሯል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Comments