ጳጉሜ 5፣2016 - በኦሮሚያ ክልል እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚመላለሱ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የኮቴ ክፍያ አማሮናል አሉ፡፡
- sheger1021fm
- Sep 10, 2024
- 1 min read
በኦሮሚያ ክልል እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚመላለሱ የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የኮቴ ክፍያ አማሮናል አሉ፡፡
በአንድ ጭነት ከ3,000 ብር በላይ እንጠየቃለን ሲሉ ቅሬታቸውን ነግረውናል፡፡
የተለያዩ ሸቀጦችንና ምርቶችን ከቦታ ቦታ የሚያጓጉዙት የከባድ መኪና ሾፌሮች እገታ፣ ግድያና ዘረፋ ሲፈጠምባቸው መቆየቱን አሽከርካሪዎቹ ያስታውሳሉ፡፡
በጂቡቲ መስመር መንግስት ቁጥጥሩን በማጠንከሩ እገታ እና ግድያው ጋብ ቢልም የኮቴ ክፍያ እየተባለ በየመንገዱ የሚጠየቁት ገንዘብ አማሮናል ይላሉ፡፡
አቶ ግርማ ተስፋዬ በድሬዳዋ መስመር እቃዎችን ጭነው የሚመላለሱ የከባድ መኪና አሽከርካሪ ናቸው፡፡
ከድሬዳዋ እስከ ሃረር ባለው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች በየ50 ኪሎ ሜትሩ በየአንዳንዱ ኬላ እስከ 700 ብር፤ በ6 ክላዎች በድምሩ ከ3,000 ብር በላይ የኮቴ ክፍያ መጠየቃቸውን ያነሳሉ፡፡

የቤተሰብ አስተዳዳሪ በመሆናችን ካለው የኑሮ ጫና ጋር ተዳምሮ አጣብቂኝ ውስጥ ገብተናል ይላሉ፡፡
በዚህ መልኩ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በደረስንበት የተጠየቅነውን ስንከፍል ቆይተናል የሚሉት አቶ ግርማ፣ አሁን የገንዘቡን መጠን ጨምረውብናል፣ የክፍያ ቦታዎችም እየተበራከቱ ነው ብለውናል፡፡
የኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር በበኩሉ በአባላቶቼ ላይ ይደርስ የነበረው እገታና ግድያ ቀንሷል፣ አሁን ያማረረን የኮቴ ክፍያ ነው፣ በተለይ የድሬዳዋ መስመር ላይ ችግሩ ይበረታል የሚሉት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ዘውዱ ናቸው፡፡
በኦሮሚያ እና በድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር የሚጠየቀው የኮቴ ክፍያ ከባድ መኪኖች መንገዱን ስለሚጎዱት፣ የተጎዳውን ለመጠገን እንደሚውል ክልሎቹ ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን መንገዱን የሚጠግነው የፌድራል መንግስቱ ነው፤ በመሆኑም ክልሎች ለዚህ ክፍያ መጠየቅ እንደማይገባቸውና ስህተት መሆኑን ለትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አስረድተን ተማምነናል ብለዋል፡፡
በመሆኑም ክልሎቹ ክፍያውን እንዲያቆሙ ሚኒስቴሩ ደብዳቤ እንደፃፈላቸውና፣ እንደሚያስቆመውም እምነት እንዳላቸው አቶ ሰለሞን ጠቁመውናል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየቱን እንዲሰጠን የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርን ጠይቀናል፣ ባለስልጣኑ በኮቴ ክፍያ ዙሪያ ከኢትዮጵያ ከባድ መኪና አሽከርካሪዎች ማህበር ጋር መነጋገሩን አረጋግጦልናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Commentaires