top of page

ጳጉሜ 5፣2016 - በአማራ ክልል በተለያዩ አካባቢዎች በሚፈፀሙ እገታዎች ስጋት ውስጥ ወድቀናል ሲሉ ነዋሪዎች ተናገሩ

በጎንደር ከተማ የፒያሣ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሸረፈዲን ኢብራሂም ‘’ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ መንቀሳቀስ ቅንጦት ሆኖብን ሳለ አሁን ደግሞ ከቤታችን መታገት መጣብን’’ ሲሉ ተናግረዋል፡፡


‘’ሰው መጠየቅ፣ ሀዘን መድረስ እና ወደ አምልኮ ስፍራ መሄድ በእገታው ምክንያት ቀርቷል’’ ብለዋል፡፡


‘’በከተማ የሚኖረው ነዋሪ ሳይቀር በእገታ ስጋት ውስጥ ወድቋል’’ የሚሉት አቶ ሸረፈዲን ‘’ነዋሪው ሲመሽ መስጋት፣ ሲነጋ ደግሞ መደሰት ውስጥ ነው’’ ሲሉ ያስረዳሉ፡፡


‘’ዛሬ ማን ተያዘ የሚለውም የነዋሪው የየዕለት ተዕለት ስጋት ሆኗል’’ ሲሉ ነግረውናል፡፡


‘’በፊት ውጪ አገር ቤተሰብ ያለው ማነው፣ ገንዘብ ያለው ማነው ብለው ነበር የሚያግቱት አሁን ግን ደሃውም እየታገተ ነው’’ ይላሉ በዚህም መሰረት ‘’ህብረተሰቡ ተጨንቆ ነው ያለው’’ ብለዋል፡፡


‘’መንግስትንም አለ ስንለው የሌለ ሆኖ እናገኘዋለን፣ የለም ስንል ደግሞ ኖሮ እናገኘዋለን ግራ የገባ ነገር ሆኖብናል’’ የሚሉት የጎንደር ከተማ የፒያሣ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሸረፈዲን ኢብራሂም ናቸው፡፡


‘’እገታው ማታም ቀንም ነው የሚፈፀመው’’ ያሉት አቶ ሸረፈዲን ‘’ኗሪው ሰርቶ ነግዶ ለመኖር ይቅርና ወደ ሃይማኖት ተቋማት እንኳን ለመሄድ ስጋት ውስጥ ወድቋል በዚህም ተጨንቅን ነው ያለነው’’ ብለዋል፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞን የይፋግ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አባት እገታው ተባብሶ መቀጠሉን ነግረውናል፡፡


ወጣቱም ሽማግሌውም የሃይማኖት አባቱ ሁሉም ስጋት ውስጥ መሆኑን አስረድተዋል፡፡


ከቀናት በፊት በይፋግ ከተማ 2 ወጣቶች ታግተው ተወስደው በ3ኛው ቀን ተገድለው መገኘታቸውንም እኚህ አባት አስረድተዋል፡፡


አቶ ጥለው ሊበን የተባሉ የክልሉ ነዋሪ በበኩላቸው ‘’በእገታው ምክንያት ወጥቶ ለመንቀሳቀስ ሰው ተቸግሯል ስጋትም ውስጥ ወድቋል’’ ብለዋል፡፡


ከቀናት በፊት የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ሪፖርት በተራዘመ የትጥቅ ግጭት ምክንያት በአንዳንድ አካባቢዎች በህግ ማስከበርና በመንግስት ህግ መዋቅር መላላት የሚፈፀሙ እገታዎችና ዘረፋዎች ነዋሪዎችን በእጅጉ እንዳማረሩ መናገሩ ይታወሳል፡፡


በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈፀመው እገታ ተባብሶ መቀጠሉን ኢሰመኮ አስረድቷል፡፡


እገታውን የሚፈፀመው ደግሞ በታጣቂ ሀይሎች፣ ለዘረፋ በተደራጁ ቡድኖችና በአንዳንድ የመንግስት የፀጥታ አካላት መሆኑን ኢሰመኮ ጠቁሞ ነበር፡፡


ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 ራዲዮ በጉዳዩ ላይ የክልሉን አመራሮች ምላሽ ለማካትት ያደረገው ተደጋጋሚ ሙከራ አልተሳካም፡፡


ከቀናቶች በፊት የክልሉ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊን ጠቅሶ ብሔራዊው የቴልቭዥን ጣበያ በሰራው ዘገባ በአማራ ክልል ከፖለቲካ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን የኢኮኖሚ አቅም አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ነዋሪዎች ከህፃናት እስከ አረጋዊያን ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች መኖራቸውን ዘግቧል፡፡


ያሬድ እንዳሻው

Comments


bottom of page