ጳጉሜ 4፣2026 - የፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈፀመ
- sheger1021fm
- Sep 9, 2024
- 1 min read
የፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ የቀብር ሥነ-ሥርዓት ተፈፀመ።
የፕሮፌሰር እንድሪያስ የቀብር ሥነሥርዓት የተፈፀመው በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተክርስቲያን ነው።
በቀብር ሥነሥርዓቱ ላይም ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ፣ የሀይማኖት አባቶች የፕሮፌሰር እንድርያስ ወዳጅ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
ከቀብር ሥነሥርዓቱ አስቀድሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ፊት ለፊት በተጣለ ድንኳን የሽኝት ሥነሥርዓት ተካሄዷል።
በዚያ የስንብት ዝግጅት ላይ ፕሬዚደንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የኦሮሚያ እና ትግራይ ክልል ፕሬዚዳንቶች ፣ የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን፣ የፕሮፌሰር እንድሪያስ ወዳጆችና ቤተሰቦች ተገኝተዋል።
ፕሮፌሰር እንድሪያስን ከወጣትነት እድሜያቸው ጀምሮ የሚያውቋቸው ጓደኞቻቸው፣ አብረዋቸው በዩኒቨርሲቲ የሰሩ ምሁራን፤ የፍልስፍና ምሁሩን በህይወት አጋጣሚ የሚያውቁትን ምስክርነት ሰጥተዋል።

በተለይ በዩኒቨርሲቲው የ9 ዓመታት የፕሬዚዳንትነት ቆይታቸው ለዩኒቨርሲቲው ማደግ ያበረከቱት አስተዋፅኦ በቅርብ አብረዋቸው የሰሩ ምሁራን የአድናቆት ቃል ሰጥተዋቸዋል።
ፕሮፌሰር እንድሪያስ ለመምህርነት ሞያ ያላቸው ፍቅር፣ ለወንድማማችነት የነበራቸው ጉልህ ቦታ፣ ሀገር ወዳድነታቸው በስንብታቸው ወቅት ተነስቷል።
የአደባባይ ምሁሩ፤ የዓድዋ ድል 100ኛ ዓመት ሲከበር፣ የአክሱም ሀውልት ወደ ሀገሩ እንዲመልስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
እድሜ እና ጤና ከቤት አውሏቸው የነበሩት ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ በሀገሪቱ ውስጥ ያለው ጦርነት፣ ረሃብ፣ መፈናቀል በእጅጉ ያሳስባቸው እንደነበር የቤተሰብ አባሎቻቸው ሲናገሩ ሰምተናል።
የአደባባይ ምሁሩ ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ የእሳት አደጋ ደርሶባቸው በህክምና ኮምፕሊኬሽን የተነሳ ህይወታቸው ማለፉንም በስንብታቸው ላይ ተነግሯል።
የካቲት 23 በ1937 ዓ.ም በአዲስ አበባ የተወለዱት ፕሮፌሰር እንድርያስ እሸቴ በአሜሪካ ሀገር ስመጥር ዩኒቨርሲቲዎች ተምረዋል፣ አስተምረዋል።
በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ(የአሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) በመምህርነት እና በፕሬዝዳንትነት አገልግለዋል።
በህገመንግስቱ ቀረፃ ወቅት ከፍተኛ ምሁራዊ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
በኢንተር አፍሪካ ግሩፕ፣ በጣና ፎረም ትልቅ ስራ መስራታቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊም አማካሪ ሚኒስትር ሆነው ሰርተዋል።
ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ በጥልቅ አሳቢነታቸው፣ በማህበራዊ ፍትህ ናፋቂነታቸው፣ አዳማጭነታቸው፣ ትዕግስተኝነታቸው ጓደኞቻቸው ያስታውሷቸዋል።
በተወለዱ 79 ዓመታቸው ነሀሴ 23/2016 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ፕሮፌሰር እንድሪያስ እሸቴ የአሉላ እንድሪያስ ወላጅ አባት ናቸው።
ንጋቱ ሙሉ
Comments