ጳጉሜ 1፣2016 - ላዳ ታክሲዎች አርጅተው የአገልግሎት ዘመናችሁ አልቋል፤ በአዲስ መተካታችሁ አይቀሬ ነው የተባሉት ከአራት ዓመት በፊት ነበር
- sheger1021fm
- Sep 6, 2024
- 1 min read
በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳና ውር ውር የሚሉት ነጭ በሰማያዊ ላዳ ታክሲዎች አርጅተው የአገልግሎት ዘመናችሁ አልቋል፤ በአዲስ መተካታችሁ አይቀሬ ነው የተባሉት ከአራት ዓመት በፊት ነበር፡፡
ለዚህ ደግሞ አሮጌዎቹ ላዳዎች በአዲስ ሲተኩ ለሾፌሮቹ መንግስት ከቀረጥ ነፃ መኪኖች እንዲያስገቡ መፍቀዱ የሚታወስ ነው፡፡
‘’ኤል አውቶ ኢንጅነሪንግ እና ትሬዲንግ ሀላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር’’ ደግሞ መኪኖቹን ከቀረጥ ነፃ እያስገባ በመገጣጠም በቅድሚያ 20 በመቶ አስከፍሎ ቀሪውን በብድር ለባለቤቶቹ እንደሚያስረክብ ቃል ገብቶ ስራ ጀምሯል፡፡
በዚህም በአራት ዓመታት ውስጥ ከ200 በላይ መኪኖች ብቻ ለሾፌሮች መሰጠቱን የማህበሩ አባላት ይናገራሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ አስመጭው 540 መኪኖችን ወደ ሀገር አስገብቶ እጣ የደረሳችሁ ሾፌሮች ውሰዱ ቢልም መኪናውን ለመውሰድ የሚያስፈልጋችሁን ቀሪ 80 በመቶ አበድራችኋለሁ ብሎ ያለው ግሎባል ባንክ ኢትዮጵያ ብድሩን ሊለቅልን አልቻለም ይላሉ፡፡
‘’የነበሩንን መኪኖች አሰወግደን አዲስ ለምንቀበለው መኪና ብዙ ገንዘብ አውጥተን የሚያስፈልጉ ነገሮችን አሟልተናል፤ ነገር ግን ባንኩ ቃል በገባልን መሰረት አበድራችኋለሁ ያለውን ባለማበደሩ ምክንያት ኪሳራ ውስጥ እየገባን ነው ሲሉ’’ ለሸገር ራዲዮ 102.1 ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህ ደግሞ ችግር ውስጥ እንድንወድቅ፣ ቤተሰቦቻችንን እንዳናስተዳድር ከማድረጉም በላይ መኪኖቹ ላይ የሚደርሰው ብልሽት ቀላል አይደለም ይላሉ፡፡
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Commentaires