top of page

ጥቅምት19፣2016 - ''የአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በተለያየ ደረጃና ጊዜ የትጥቅ ግጭት ተካሂዶባቸዋል'' ኢሰመኮ

በአማራ ክልል የቀጠለው የትጥቅ ግጭት በአየር መሣሪያ (ድሮን) ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች በደረሰ ጥቃት በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት መድረሱን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ተናገረ፡፡


ኮሚሽኑ ‘’ለወራት የቀጠለው የትጥቅ ግጭት ዐውድ እና አሉታዊ የሰብአዊ መብቶች እንድምታው’’ በሚል ርዕስ በዛሬው እለት መግለጫ አውጥቷል፡፡


ኮሚሽኑ ግጭቱ በሰብአዊ መብቶች እና በማኅበራዊ እንቅስቃሴ ላይ ያስከተለውን አሉታዊ ውጤት በቅርበት መከታተሌን ቀጥያለሁ ብሏል፡፡


በተለይም የሚመለከታቸውን መንግሥታዊ ኃላፊዎችን፣ በግጭቱ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎችን፣ የዐይን ምስክሮችን፣ ተጎጂዎችንና የተጎጂዎች ቤተሰቦችን በማነጋገር መረጃዎችንና ማስረጃዎችን ሲያሰባስብ መቆየቱን ጠቅሷል።


ይህ መግለጫ ይፋ እስከተደረገበት ጊዜ ድረስ በክልሉ ብዙ ወረዳዎች ውስጥ የትጥቅ ግጭት የተከሰተ ሲሆን ከሐምሌ ወር 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ባለው ጊዜ ውስጥ የአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች በተለያየ ደረጃና ጊዜ የትጥቅ ግጭት ተካሂዶባቸዋል ሲል አስረድቷል።


በተጨማሪም እነዚህ አካባቢዎች ወይም ወረዳዎች በአንድ ወቅት በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች፣ በሌላ ወቅት በታጣቂው ቡድን (በተለምዶ ፋኖ በመባል የሚታወቀው) ቁጥጥር ሥር ውለዋል ሲልም ተናግሯል።


የትጥቅ ግጭቱ በአንዳንድ አካባቢዎች በከባድ መሣሪያ እና አልፎ አልፎ በአየር(ድሮን) ድብደባ ጭምር የታገዘ መሆኑንም ኢሰመኮ አስረድቷል።


በግጭቱ ዐውድ የአየር(ድሮን) መሣሪያን ጨምሮ በከባድ መሣሪያዎች ጥቃት የተነሳ በሲቪል ሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት የደረሰ ሲሆን ሰዎች መኖሪያ አካባቢያቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገደዋል ብሏል።


ኮሚሽኑ ለዚህም አስረጂ እንዲሆነው ምሳሌ ጠቅሷል፡፡


በሰሜን ሸዋ ዞን በረኸት ወረዳ ‘መጥተህ ብላ’ ከተማ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም በተፈጸመ የድሮን ጥቃት የአንድ ዓመት ከሰባት ወር ሕፃንን ጨምሮ በርካታ ሲቪል ሰዎች እንደተገደሉ እና የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል፡፡


በደብረ ማርቆስ ከተማ ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ደግሞ ቢያንስ 8 ንፁሀን ሰዎች እንደተገደሉ እንዲሁም በደንበጫ ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. በከባድ መሣሪያ ድብደባ ምክንያት ንፁሀን ሰዎች ላይ የሞትና የአካል ጉዳት መድረሱን ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎችና የዐይን ምስክሮች አስረድተዋል ተብሏል።


በአንዳንድ አካባቢዎች ጥቃትን አልያም ግጭትን በመሸሽ ነዋሪዎች ሙሉ በሙሉ ከቀያቸው ተፈናቅለው በአሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ መቻሉን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በሪፖርቱ ተናግሯል።


በምንጃር ወረዳ የ’አውራ ጎዳና’ ጎጥ ነዋሪዎች ከመስከረም 6 ቀን 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ከቀያቸው ተፈናቀለው ቢያንስ 3,000 የሚሆኑት ‘አሞራ ቤቴ’ ቀበሌ በሚገኝ አንድ ትምህርት ቤትና ክፍት ሜዳ ላይ (በዛፍ ሥር) ተጠልለው እንደሚገኙ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡


ሌሎች ቁጥራቸው ያልታወቀ መተሃራና አዋሽን ጨምሮ ወደ የተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለዋል፣ ለተፈናቃዮች የተወሰነ ድጋፍ በማኅበረሰቡና እና በአንድ ተራድዖ ድርጅት የተደረገ ቢሆንም፣ በቂ ባለመሆኑ በአሳሳቢ ሁኔታ እንደሚገኙ ተረድቻለሁ ብሏል።


የነዋሪዎችን መፈናቀል ተከትሎ ሰብላቸው እንደወደመ፣ ንብረታቸው እንደተዘረፈ፣ የቤቶቻቸው ጣራያ እና በር እየተነቀለ እንደተወሰደ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ቤቶቻቸውን ከአጎራባች ክልል በመጡ ኃይሎች በኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ጭምር ማፍረስ እንደተጀመረ ኢሰመኮ ያነጋገርኳቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እና የመንግሥት ኃላፊዎች አስረድተውኛል ሲል ጠቅሷል።


በተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች የሚፈጸሙ ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች አሳሳቢነት ኮሚሽኑ በመስከረም 4 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ መጥቀሱን አስታውሶ አሁንም በመንግሥት የጸጥታ ኃይል አባላት የሚፈጸሙ ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎች መቀጠላቸውን ኢሰመኮ ተዓማኒ መረጃዎችን እየተቀበልኩ ነው ብሏል።


የመንግሥት የጸጥታ አካላት በመንገድ ላይ ወይም ቤት ለቤት ፍተሻ በማድረግ ከያዟቸው በርካታ ሲቪል ሰዎች ውስጥ “ፋኖን ትደግፋላችሁ፣ ለፋኖ መረጃ ትሰጣላችሁ፣ መሣሪያ አምጡ፣ የተኩስ ድምጽ ስለተሰማበት አቅጣጫ መረጃ ስጡ” በሚልና ይህንን በመሰሉ ምክንያቶች ከሕግ ውጭ የሆኑ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያሳዩ ተዓማኒ መረጃዎች ለኮሚሽኑ ደርሰውታል ሲል ኢሰመኮ በመግለጫው አስፍሯል።


እንደማሳያ በባሕር ዳር ከተማ ‘ሰባታሚት’ አካባቢ መስከረም 29 እና 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ሦስት ወንድማማቾችን ጨምሮ በርካታ ንፁሀን ሰዎች፣ በሰሜን ጎጃም ዞን ‘አዴት’ ከተማ መስከረም 29 ቀን 2016 ዓ.ም. ፍልሰታ ደብረ ማሪያም የሚኖሩ 12 የአብነት ተማሪዎችን ጨምሮ ሌሎች ንፁሀን ሰዎች በምሥራቅ ጎጃም ዞን ‘አማኑኤል’ ከተማ ጥቅምት 3 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢያንስ 8 ንፁሀን ሰዎች በቤት ለቤት ፍተሻ እንደተገደሉ ኢሰመኮ ተናግሯል።


በሌላ በኩል በየደረጃው የሚገኙ ሲቪል የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች፣ ግድያዎችና እገታዎች በታጠቁ ኃይሎች ተፈጽመዋል ብሏል ኢሰመኮ።


መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም. የአማራ ክልል ምክር ቤት የሕግ፣ ፍትሕና አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢን ጨምሮ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከባሕር ዳር ወደ ደብረ ታቦር ሲሄዱ አለምበር ከተማ አካባቢ በታጣቂዎች ተገድለዋል ብሏል ሪፖርቱ።


በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች ማረሚያ ቤቶችና ፖሊስ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ታራሚዎችና ተጠርጣሪዎች አምልጠዋልም ብሏል፡፡


ኮሚሽኑ አደርኩት በላው ክትትል በተለይም በመንግሥት ተቋማት ጭምር በሚደርሱት መረጃዎች መሠረት በግጭቱ ዐውድ የሚፈጸሙ የአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች በጣም አሳሳቢ እና በአፋጣኝ ተገቢው ምርመራ ተደረጎ እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል ብሏል፡፡


የጤና ተቋማት መድረስ የቻሉትን ተጎጂዎች ቁጥር ብቻ መሠረት በማድረግ፣ ከሐምሌ ወር 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ይህ መግለጫ እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ቢያንስ 200 የአስገድዶ መድፈር ተጎጂዎች በጤና ተቋማት ተመዝግበዋል፤ ከተጎጂዎች መካከልም የሀገር ውስጥ ተፈናቃይ እና የጤና ባለሞያ ሴቶች ጭምር ይገኙበታል ሲል አስረድቷል።


ከትጥቅ ግጭቱ መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሲቪል ሰዎች እና የሲቪል የንግድ እና የመሠረተ ልማት ተቋማት ላይ ዝርፊያ፣ የማሳ ላይ ሰብል ውድመት ጨምሮ በሲቪል ሰዎች፣ በሕዝብ እና በመሠረተ ልማት ላይ ጉዳት ደርሷል።


ሕፃናት ከትምህርት ውጪ መሆናቸው እና በአንዳንድ አካባቢዎች የትምህርት ተቋማት ለወታደራዊ አገልግሎት መዋላቸው ኢሲመኮ በመግለጫው ተናግሯል፡፡


የማኅበራዊ አገልግሎትና የሕክምና ተቋማት አገልግሎት በማቋረጣቸው ምክንያት፤ ነዋሪዎችን፣ በአማራ ክልል የተጠለሉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮችን እና ስደተኞችን ለተባባሰ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚያጋልጥ ነው ብሏል።


የአዴት ሆስፒታል በደረሰበት ዘረፋና ጉዳት አገልግሎት መስጠት አቁሟል የተባለ ሲሆን የፍኖተሰላም ሆስፒታል በደረሰበት ጥቃት እንዲሁም በባሕር ዳር የሚገኘው ጥበበ ግዮን ሆስፒታል በሠራተኞች፣ ታካሚዎችና አስታማሚዎች ላይ በደረሰው ወከባ፣ ድብደባና እስራት ምክንያት አገልግሎት ተቋርጦ ከነበረባቸው የጤና ተቋማት መካከል ይገኙበታል ተብሏል።


በተለያየወቅት በአማራ ክልል አብዛኛው አካባቢዎች ተግባራዊ በተደረገው የእንቅስቃሴ ገደብ እና የሰዓት እላፊ እንዲሁም በጸጥታ መደፍረስ የተለያዩ ወረዳዎችን የሚያገናኙ የመንገድ መጓጓዣዎች በመቋረጣቸው አልያም ውስን በመሆናቸው ምክንያት፣ የንግድ እና የማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በፈጠረው ተጽዕኖ ነዋሪዎች ለአቅርቦት እጥረት እና ለዋጋ ንረት እንዲሁም ለተያያዥ ችግሮች ተዳርገዋል።


የተለያዩአምራች አካባቢዎች ምርት ያቋረጡ ሲሆን በገንዘብ ዝውውር ላይ የተጣለው ገደብን ጨምሮ በአንዳንድ ተቋማት የደመወዝ ክፍያ መቋረጥም ነዋሪዎችን ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ዳርጓል።


በተጨማሪምበተለይም በሰሜን ጎንደር እና በዋግኅምራ አካባቢዎች በተደራራቢ ምክንያቶች በርካታ ሰዎች አስቸኳይ የምግብ ድጋፍ የሚሹ መሆኑ ኢሰመኮ ተናግሯል።


የኢሰመኮዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “ኮሚሽኑ ግጭቱን በዘላቂነትለመፍታት ለሁሉም ሰላማዊ አማራጮች አሁንም ቅድሚያ መስጠትን ጨምሮ፤ ተፋላሚ ወገኖች ንፁሀን ሰዎችንና ንብረቶችን፣ የሕዝብ አገልግሎቶችን እና መሠረተ ልማቶችን በማናቸውም ሁኔታ ዒላማ እንዳያደርጉ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ የታጠቁ ኃይሎች አባላትና ሌሎች ተጠርጣሪዎችም ሁኔታ በሕጋዊ አግባብ ብቻ እንዲስተናገድ፤ በተለይም የአስገድዶ መድፈር ወንጀል እና ከሕግ ውጭ የተፈጸመ ግድያ በአስቸኳይ በማጣራት ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና የማኅበራዊ አገልግሎቶች በተቻለ ፍጥነት እንዲቀጥሉ እንዲደረግ” አሳስበዋል፡፡


ተፈናቃዮችአስፈላጊው የሰብአዊ ድጋፍ በአስቸኳይ እንዲደርሳቸው እንዲደረግ፤ ለመፈናቀል የዳረጋቸው ምክንያት እልባት አግኝቶ በዘላቂነት ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻች ዋና ኮሚሽነሩ ጥሪ ማቅረባቸውን በመግለጫ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሸገርንወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz



Comments


bottom of page