በግብርናው ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶች ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት እየሰራሁ ነው ሲል ሰስተነብል ገሮዊንግ አፍሪካስ ፉድ ሲስተም (Sustainable growing Africa’s food systems/AGRA) የተሰኘ ድርጅት ተናገረ፡፡
ሴቶች በግብርና ዘርፍ ወደ ፊት እንዲወጡ እና ያሉባቸው ችግሮች እንዲቀረፉላቸው ድርጅቱ ቫልዩ ፎር ኸር (VALUE4HER) በተሰኘ ተነሳሽነት ሴቶችን ለማገዝ እየሰራ መሆኑ ተነግሯል፡፡
የሀብት ባለቤት አለመሆናቸው፣ የፖሊሲ ክፍተት መኖሩ፣ የብድር አቅርቦት አለመመቻቸት እና ሌሎችም ችግሮች ሴት ገበሬዎች ከሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶች መካከል ነው ተብሏል፡፡
VALUE4HER በሴቶች የሚመሩ የግብርና ንግዶችን ለማበረታታት እና ፍትሃዊ እድገትን ለማምጣት ይሰራል የተባለ ሲሆን በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በዘርፉ የተሰማሩ ሴቶችን ለመደገፍ ስራዎችን መከወን ጀምሯል ተብሏል፡፡
በዚህም በመጀመሪያ ፕሮግራሙ 2,000 በግርናው ዘርፍ የተሰማሩ ሴቶችን መደገፍ ላይ ይሰራል ያሉት ኢትዮጵያ ውሜን ኢን ኮፊ (Ethiopia women in coffee) ዳይሬክተር ሳራ ይርጋ ለነዚህም ሴቶች የአቅም ግንባታ መስጠት፣ ብድር ማመቻቸትን ጨምሮ ሌሎች ድጋፎች ያደርጋል ብለዋል፡፡
በአፍሪካ በግብርናው ዘርፍ ያሉ ሴት ሥራ ፈጣሪዎችን መደገፍ የገበያ ሰንሰለት መፍጠር፣ የብድር አቅርቦት ማመቻቸትን ጨምሮ ሌሎች ግብአቶች ማሟላት ላይ የሚሰራው እና በAGRA ተነሳሽነት ሴቶችን የሚደግፈው VALUE4HER ፕሮጀክት በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ነው ተብሏል፡፡
በዘርፉ የተሰማሩት ሴቶች የሀብት ባለቤት አለመሆናቸው በሚከውኑት ስራ ልክ እንዳያድጉ አድርጓቸዋል የሚሉት ደግሞ የAGRA የሀገር ውስጥ ፕሮግራም ሀላፊ የሆኑት ኒኮላስ ኦባሬ በዘርፉ ያለ የፖሊሲ ክፍተትም ሌላኛው ችግራቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
በ VALUE4HER ለመጀመሪያ ጊዜ የሚያሰናዳው ይህ የቀዳሚው ዙር ስልጠና የማጠናቀቂያ ጊዜው በዘርፉ በተሰማሩ ሴቶች የሚወሰን እንደሚሆን ተነግሯል፡፡
በዚህ ስልጠና ለመሳተፍ የሚያስፈልገውም ምርቶቻቸውን ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ ገበያ የሚያቀርቡ በግብርናው ዘርፍ የመስራት ፍቃድ ያላቸው መሆናቸው ብቻ በቂ ነው ተብሏል፡፡
ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ ይህንን ማስፈንጠሪያን ይጫኑ.. https://tinyurl.com/5n7w73c3
ፋሲካ ሙሉወርቅ
Comments