top of page

ጥቅምት 5፣2017 - ዳሸን ባንክ በ2016 በጀት ዓመት 6.4 ቢሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ አገኘሁ አለ።

በተቀማጭ የገንዘብ መጠን የ30.9 ቢሊዮን ብር እድገት አስመዝግቤአለሁ ያለው ባንኩ፤ አጠቃላይ ተቀማጭ የገንዘብ መጠኔ ደግሞ 145.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል ብሏል።


ባንኩ ይህንን ያለው የባለአክሲዮኖች 31ኛ መደበኛና 26ኛ አስቸኳይ ጉባኤውን በዛሬው እለት ባካሄደበት ወቅት ነው።


ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት፣ በተለያዩ ቦታዎች የቀጠሉ ግጭቶችና የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረት በባንክ ኢንዱስትሪው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን የተናገሩት የባንኩ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ ዱላ መኮንን በበጀት ዓመቱ የባንክ ኢንዱስትሪው የገንዘብና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ውስጥ እንደነበር ተናግረዋል።

ያም ሆኖ #ዳሽን_ባንክ ችግሮችን ተቋቁሞ የደንበኞቹን ፍላጎት ለሟሟላት ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ዱላ የባንኩ አጠቃላይ ሃብት የ27 በመቶ ዕድገት በማስመዝገብ 183.7 ቢሊየን ብር መደረሱን ተናግረዋል።


ባለፈው በጀት ዓመት 1.44 ሚሊየን አዳዲስ ደንበኞችን ማግኘት ተችሏል ይህም ለባንኩ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት አስተዋፅኦ አለው ያሉት ደግሞ የባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አስፋው አለሙ ሲሆኑ በአሁኑ ወቅት ከ6.7 ሚሊየን በላይ ደንበኞች መኖራቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪ ዳሽን ባንክ ከብሪቲሽ ኢንተርናሽናል ኢንቨስትመንት እና ከኔዘርላንድስ የልማት ባንክ ጋር በፈጠረው አጋርነት የ40 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ እንዲያገኝ አድርጎታል ያሉ ሲሆን በሌላ በኩል ከአፍሪካ ልማት ባንክ የ40 ሚሊየን ዶላር የንግድ ልውውጥ ዋስትና ፈንድ ማግኘቱንም አቶ አስፋው ሲናገሩ ሰምተናል።


የሰላም እጦት ባሉባቸው አካባቢዎች ያሉ ቅርንጫፎችን መዝጋት፣ የዋጋ ግሽበት፣ የኑሮ ውድነት፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትን ጨምሮ ሌሎችም ባንኩ በበጀት ዓመቱ ገጥሞኝ ነበር ካላቸው ችግሮች መካከል ነበሩ ተብሏል።


ፋሲካ ሙሉወርቅ

Kommentare


bottom of page