top of page

ጥቅምት 4 2018ኢትዮጵያ በባህር ላይ የተለያዩ ስራዎችን የሚከውኑ 2,600 የማሪታይም መሀንዲሶችን አሰልጥና ለውጭ ገበያ አቅርባለች ተባለ።

  • sheger1021fm
  • Oct 14
  • 1 min read

ree

የባህር ባለሞያዎቹን እያሰለጠነ የሚገኘው የባህርዳር ዩኒቨርስቲ ሲሆን በዩኒቨርስቲው ሰልጥነው በውጭ ሀገራት በተለያዩ የስራ እርከን ተቀጥረው እየሰሩ መሆኑ ተነግሯል።


የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት መንገሻ አየነ(ዶ/ር) ሰልጥነው በውጪ ሀገራት ከተቀጠሩት መካከልም 26ቱ በአለም ትልልቅ የዘርፉ ተቋማት በከፍተኛ ሀላፊነት፣ አማካሪነት እና ባለሞያነት እየሰሩ እንደሆነም አስረድተዋል።


ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ከተለያዩ የሀገሪቱ ዩኒቨርሲቲዎች በሜካኒካል እና ኤሌክትሪካል ምህንድስና የተመረቁ ምሩቃንን መልምሎ ለ6 እና ለ9 ወራት በማሰልጠን ነው የማሪታይም ዘርፍ ባለሞያዎችን እያበቃ ያለው ተብሏል።


የማሪታይም መሀንዲሶቹ የሚያሰለጥኗቸ፤ የውጪ ሀገራት ዜጎች መሆናቸውንና ስልጠናውም አለም አቀፍ ስታንዳርድ ያሟላ ነው ሲሉ መንገሻ አየነ (ዶ/ር) ተናግረዋል።


ባህርዳር ዩኒቨርስቲ ይህንን ስራ ከጀመረ 12 ዓመታት አስቆጥሯልም ብለዋል።


ዩኒቨርስቲው በተለይም ዋይሲኤፍ (YCF) ከተሰኘ ድርጅት እና ከኢትዮጵያ ማርታይም ባለስልጣን ጋር በአብሮነት እየሰራ እንደሆነና የቅበላ አቅሙ ለማሳደግ ማለሙንም ጠቁመዋል ፕሬዘዳንቱ።


ይህ የተነገረው ከዛሬ ጥቅምት 4 ጀምሮ ለ3 ተከታታይ ቀናት በአዲስ አበባ ''ዘ አፍሪካ ማሪታይም ኮንፈረንስ 2025'' በማስመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት መድረክ ላይ ነው።


ኮንፈረንሱ፤ ለአፍሪካ የባህር አጠቃቀም መሰረት የሚጥል ነው ሲባልም ሰምተናል፡፡


በአለም አቀፍ የባህር ላይ ጭነት ማጓጓዣ ኢንዱስትሪ ውስጥ ያሉ መሪዎች እንደሚሳተፉበት ተነግሯል።


የኮንፈረንሱ ዓላማ የፖሊሲ እና አጋርነትን ለማቀራረብ፣ አፍሪካ ለዓለም አቀፉ የባሕር ላይ ኢኮኖሚ ቋሚ አበርክቶ እንዳላት ለማሳየት ያለመ ነው ሲባል ሰምተናል።


የአፍሪካ የባሕር ላይ ጉባኤ ሰብሳቢና የዋይ ሲ ኤፍ ማኒንግ ሊሚትድ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍራንስ ጆበርት፤ ኮንፈረንሱ አፍሪካ ዘመናዊ፣ ተወዳዳሪና ሁሉን ያካተተ የባሕር ላይ የሰው ኃይል

ለመገንባት በጋራ በምታደርገው ጥረት በትልቁ የሚረዳትም ነው ብለዋል።


ኢትዮጵያ የአስተናጋጅነት ሚና መውሰዷ፤ በአፍሪካ የባሕር ላይ የሥልጠና ተቋም (EMT) እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ላይ የልህቀት ማዕከል በኩል በባሕር ላይ ትምህርት ላይ በዘርፉ እየሰራችው ያለ ስራ እንደ አንድ ምክንያት ተጠቅሷል።


ኮንፈረንሱ፤ ዋይ ሲ ኤፍ ማኒንግ ሊሚትድ ከኢትዮጵያ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እና ከኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ጋር በአጋርነት ያዘጋጁት ነው ተብሏል።


ማንያዘዋል ጌታሁን

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page