top of page

ጥቅምት 4፣2017 - ''የውጪ ሀገራት ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ሀገሪቱ በሰራችው ማስታወቂያ አይደለም'' የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር

የውጪ ሀገራት ቱሪስቶች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት ከሌሎች ጎብኚዎች ከሰሙት መረጃ ተነስተው እንጂ ሀገሪቱ በሰራችው ማስታወቂያ አይደለም ሲል የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ተናገረ፡፡


ማህበሩ እንዳለው በየጊዜው ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ቱሪስቶች ስለ ኢትዮጵያ ያላቸው መረጃ ባለሙያዎቻችን ሲጠይቋቸው አብዛኛዎቹ ስለ ኢትዮጵያ የሚያውቁት ነገር የለም ብሏል፡፡


#የኢትዮጵያ_ቱሪስት_አስጎብኚ_ባለሙያዎች_ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ አቤል መኮንን አብዛኛዎቹ የውጪ ሀገራት ጎብኚዎቻችን ስለ ኢትዮጵያ መረጃ የሚሰሙት ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ከጎበኙ ጓደኞቻቸው አልያም ተጓዦች ነው፡፡


ይህም የሚያሳየው እራስን በማስተዋወቅ ላይ ከፍተኛ ድክመት እንዳለብን ነው ሲሉ አቶ አቤል ነግረውናል፡፡


እንደ ሩዋንዳ ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኬንያ የመሳሰሉ ሀገራት እራሳቸውን በአለም አቀፍ ሚዲያ እና በሌሎች አማራጮች ሃገራቱ ያላቸው የ #ቱሪዝም ፀጋዎች ሲያስተዋውቁ ይስተዋላል ያሉት አቶ አቤል ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ድክመቶች ይታያሉ ብለዋል፡፡

ይህንን ለማስተካከል መንግስት በቱሪዝም ዘርፍ ከተሰማሩ ባለድርሻ አካላት ጋር ተነጋግሮ በጋራ ራስን በተደራጀ መንገድ ማስተዋወቅ የሚቻልበትን ስራ መስራት አለበት ሲሉ ይመክራሉ፡፡


ከዚህ ቀደም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡት የውጪ ሃገራት #ቱሪስቶች መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ የነበራቸው ጎብኚዎች ነበሩ ያሉት የኢትዮጵያ ቱሪስት አስጎብኚ ባለሙያዎች ማህበር ዋና ፀሐፊ አቶ አቤል መኮንን ለዚህ ምክንያቱ ቅንጡ ሆቴሎች በቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎች ባለመኖራቸው ነበር፡፡


አሁን በገበታ ለሀገርና በገበታ ለሸገር ፕሮጀክቶች ይህ ተቀርፏል ሰላም ሲመጣ እነዚህ ጎብኚዎች የመሳብ አቅም አለን ሲሉ ነግረውናል፡፡


የቱሪዝም ሚኒስቴር በበኩሉ የቱሪዝሙ መስህቦችን ለማስተዋወቅ ከመገናኛ ብዙሃን በተጨማሪ ማህበራዊ ትስስር ገፆችን እየተጠቀምኩኝ ነው ያለ ሲሆን አሁን ትልቁ እንቅፋት እንደ ሀገር ያለው የፀጥታ ችግር ነው በማለት ከዚህ ቀደም ለሸገር ሬድዮ ተናግሯል፡፡


በረከት አካሉ

Comments


bottom of page