ጥቅምት 3 2018 - ለ2 ወር በከፊል ዝግ ሆነዉ የቆዩት ፍ/ቤቶች ከዛሬ ጀምሮ ወደ መደበኛ የችሎት አገልግሎት ይመለሳሉ ተባለ
- sheger1021fm
- Oct 13
- 1 min read
መደበኛ የችሎት አገልግሎቱም በቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ፈጣንና ጥራት ያለዉ የዳኝነት ስራ የሚሰራበት እንዲሆን ዝግጅት ተደርጓል ተብሏል።
ይህ የተነገረው የ2018 ዓ/ም የመደበኛ የችሎት አገልግሎት ማስጀመሪያ ሥነ-ስርዓት ላይ ነዉ።
ነፃና ገለልተኛ የዳኝነት ስርዓትን ለማሳደግ፣ ተዓማኒነት ያለዉ የፍትህ ስርዓት ለመዘርጋት፣ በቴክኖሎጅ የተደገፈ አገልግሎት ከተጠያቂነት ጋር እውን ማድረግ አንደሚገባ ተጠቁሟል።
ፍርድ ቤቶች በየዓመቱ ከነሀሴ 1 እስከ መስከረም 30 ድረስ በከፊል ዝግ ሆነው ቆይተዉ ጥቅምት 1 መደበኛ ስራቸውን እንደሚጀምሩ ይታወቃል።
ዘንድሮም ለሁለት ወር በከፊል ዝግ ሆነዉ የቆዩት ፍርድ ቤቶች ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 03/2018 ዓ.ም መደበኛ የችሎት አገልግሎት ይጀምራሉ ተብሏል።
በማስጀመሪያ ስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ነፃና ገለልተኛ የዳኝነት ስርዓትን ለማሳደግ፣ ተዓማኒነት ያለው የፍትህ ስርዓት ለመዘርጋት፣ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አግልግሎት ከተጠያቂነት ጋር እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ከፈጣሪ በታች ለዜጎች ፍትህን የማስፈን ስልጣንና ሀላፊነት የተሰጣቸው ለፍርድ ቤቶች ስለሆነ ዳኞች ለፈጣሪያቸውና ለህሊናቸው ታምነዉ የፍትህ ስራዓቱን በማሻሻል ተዓማኒነት ያለው የዳኝነት ስራ አንዲጎለብት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በተለይም ከሙስና የተላቀቁ፣ በግልጽነት፣ በታማኝነት፣ በፍጥነትና በጥራት ስራቸዉን ብቻ የሚከውኑ ተቋማትን ለመፍጠር መሰራት አለበት ብለዋል።
አፈ-ጉባኤው ታገሰ ጫፎ የዳኝነት አሰጣጥ ፍጥነትን መጨመር፣ የጥናትና ምርምር አቅምን ማሳደግ፣ የዳኝነት ብቃትን ከፍ ማድረግ፣ የዳኝነትን ነጻና ገለልተኛ መርህን ማረጋገጥ አንዲሁም ሙሉ በሙሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን መዘርጋት እንደሚገባም አንስተዋል።
እነዚህ ተግባራት በ2018 ዓ/ም ትኩረት ተደርጎ ይሰራባቸዋል ብለዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ-ቤት ፕሬዘዳንት ቴዎድሮስ ምህረት በበኩላቸዉ በ2017 የዳኝነትን ግልፅነትና ተጠያቂነት ለማረጋገጥ፣ የተገልጋዩን ፍላጎት ለማሟላትና ፍትህን ለማስፈን ብዙ ስራዎች አንደተሰሩ አብራርተዋል።
ዳኞች ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲያገለግሉ የሚያግዙ የህግ ማዕቀፎችን በማፅደቅ ወደ ስራ እንዲገቡ አድርገናል ብለዋል።
ሰኞ በሚጀመረዉ የ2018 ዓ.ም መደበኛ የችሎት አገልግሎትም በቴክኖሎጂ በመታገዝ ፈጣንና ጥራት ያለው የዳኝነት ስራን ለመከወን በትኩረት አንደሚሰራ አቶ ቴዎድሮስ ተናግረዋል።
ገዛ ጌታሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
👇👇👇
🌐Website፡ https://www.shegerfm.com/
🎥YouTube https://tinyurl.com/37tux478
🟦Telegram https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📘Facebook፡ https://tinyurl.com/4tx8t8wm
💬WhatsApp ፡ https://tinyurl.com/ycxjmm3s
👔LinkedIn ፡ https://tinyurl.com/tyfaekvx












Comments