ጥቅምት 29፣2017 - የውንብድና እና የቅሚያ ወንጀል ሲፈፅሙ የቆዩ 17 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ተናገረ
- sheger1021fm
- Nov 8, 2024
- 1 min read
የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ መስለው በተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ የውንብድና እና የቅሚያ ወንጀል ሲፈፅሙ የቆዩ 17 ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ ተናገረ።
የተለያዩ ንብረቶችም ከተጠርጣሪዎቹ እጅ ላይ በኤግዚቢትነት ይዣለሁም ብሏል ፖሊስ።
በየካ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የአድዋ ድልድይ አካባቢ ፖሊስ ጣቢያ፤ ''በተሽከርካሪ በመንቀሳቀስ የሃይል ተግባር በመጠቀም በተለያዩ ግለሰቦች ላይ የ #ቅሚያ እና የ #ውንብድና ወንጀል ፈፅመዋል'' በሚል ተጠርጥረው የተያዙ 17 ግለሰቦች ምርመራ እየተጣራባቸው እንደሚገኝ ተናግሯል።

''ተጠርጣሪዎቹ በሚኒባስ ተሽከርካሪ እየተንቀሳቀሱ #ምሽት ላይ አንድን ግለሰብ ከቦሌ ጌታሁን በሻህ ህንፃ አካባቢ ጭነው ከወሰዱ በኋላ አመቺ ቦታ ሲደርሱ የግለሰቡን እግር በጫማ ገመድ አስረው እና በስለት አስፈራርተው ሞባይል ስልክ እና ጥሬ ገንዘብን ጨምሮ በአጠቃላይ 21,500 ብር የዋጋ ግምት ያላቸውን ንብረቶች ወስደው ተሰውረዋል'' ሲልም ተናግሯል፡፡
ፖሊስ ባደረገው ክትትል ወንጀሉ የተፈፀመበትን ተሽከርካሪ በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡
የወላጆቹ በሆነው ተሽከርካሪ በቀኑ ክፍለ ጊዜ የትራንስፖርት አገልግሎት ሲሰጥ ውሎ ምሽት ላይ እስከ 10,000 ብር የሚደርስ ገንዘብ እየተቀበለ መኪናውን አሳልፎ ለወንጀል ፈፃሚዎቹ ሲሰጥ የነበረ ግለሰብንም በቁጥጥር ማዋሉን ፖሊስ አስረድቷል።
ተጠርጣሪዎቹ ከምሽቱ አንድ ሰዓት እስከ አራት ሰዓት ባለው ጊዜ ውስጥ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች እና አካባቢዎች እየተንቀሳቀሱ ወንጀሉን ሲፈፅሙ የቆዩ እንደሆኑ ጠቁሟል።
በለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና በሌሎች ፖሊስ ጣቢያዎች ተጨማሪ የምርመራ መዝገብ የተደራጀባቸው ስለመሆናቸው ፖሊስ አስረድቷል።
34 የተለያዩ አይነት ሞዴል ያላቸው ሞባይል ስልኮች፣ ላፕቶፕ ኮምፒውተር እና ሌሎች ልዩ ልዩ ንብረቶች በተጠርጣሪዎቹ እጅ ላይ ተገኝተው የምርመራው ስራ መቀጠሉ ፖሊስ ተናግሯል፡፡
Kommentare