top of page

ጥቅምት 29፣ 2017 - የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የአትክልት እና የሰብል ምርቶችን የዋጋ ተመን ማሳወቅ እጀምራለሁ አለ

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከመጭው ሳምንት ጀምሮ የአትክልት እና የሰብል ምርቶችን የዋጋ ተመን ማሳወቅ እጀምራለሁ አለ፡፡


ምርቶቹ የትኞቹ ክፍለ ከተሞች ላይ እንደሚገኙ እና የዋጋ ተመናቸውን ጨምሮ በማህበራዊ ትስስር ገፁ ላይ ማሳወቅ እጀምራለሁ ማለቱን ሰምተናል፡፡


ይህም የዋጋ ዝርዝር እና የሸቀጦቹ ዓይነት በሳምንት ሁለት ቀን ማለትም ማክሰኞ እና አርብ ቢሮው እንደሚያሳውቅ የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ሀላፊ አቶ ፍሰሀ ጥበቡ ተናግረዋል፡፡


ከዚህ ቀደም ቢሮው በከተማዋ ነዳጅ የሚገኝበትን ማደያ ለአሽከርካሪዎች ሲያሳውቅ መቆየቱን የተናገሩት አቶ ፍሰሐ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ የአትክልት እና የሰብል ምርቶች ላይም ተግባራዊ እንደሚያደርግ ተናግሯል፡፡


ሌላኛው ቢሮው ከሚሰራቸው ስራዎች መካከል አቅርቦት እና ፍላጎትን ተመጣጣኝ ማድረግ ላይ ይሰራል የተባለ ሲሆን የገበያ ማዕከላትን ማስፋፋትን እና ማዘመን ሌላኛው ተግባሩ ነው፡፡


በተጨማሪም በከተማዋ በየነዳጅ ማደያዎቹ ረጃጅም ሰልፍ እንዳይኖር እና አሽከርካሪዎች ነዳጅ ፍለጋ እንዳይንከራተቱ የሚያግዛቸውን መረጃ በየቀኑ እየሰጠሁ ነው ብሏል፡፡


የነዳጅ ማደያዎች በእለቱ የተሽከርካሪዎች ናፍጣና ቤንዚን አቅርበው አገልግሎት የሚሰጡ የትኞቹ ናቸው የት አካባቢ ነው የሚለውን ለተጠቃሚው በማሳወቅ ከእንግልት እንዲድኑ እያደረኩ ነው ሲል ቢሮው አስረድቷል፡፡


ቢሮው ይህንን ዓይነት መረጃ ለመስጠት ያስፈለገው ነዳጅ እያላቸው የለምንም የሚሉት ላይ የቁጥጥር ስራ ለመስራት እንዲያመች መሆኑን የሚናገሩት የቢሮው ምክትል ሀላፊ አቶ ፍሰሀ ጥበቡ በተጨማሪም አሽከርካሪዎች ነዳጅ ፍለጋ እንዳይደክሙ ነው ይላሉ፡፡


ምርቶች ቀጥታ ከአምራቹ ወደ ተጠቃሚው እንዲደርስ በማድረግ የነዋሪው ችግር የሆነውን የሸቀጦች ዋጋ መናር ለመቆጣጠር የሚሰራው የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ህገ-ወጥ ደላሎችን እና ምርት ከዝነው በማስቀመጥ ለዋጋ መጨመር ምክንያት የሚሆኑ ነጋዴዎችን እየተቆጣጠርኩ ነው ብሏል፡፡


ፋሲካ ሙሉወርቅ

Comments


bottom of page