top of page

ጥቅምት 29፣ 2017 - በኢትዮጵያ ያሉ 36 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ስራቸውን ለመደገፍ ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተደረገ

ከአውሮፓ ህብረት በተገኘ የ800 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ በኢትዮጵያ ሰላምን ለማስፈንና ግጭቶችን በውይይት ለመፍታት የሚያደርጉትን ጥረት ለመደገፍ ይሰራል የተባለ የ5 ዓመት ፕሮጀክት ይፋ ሆኗል፡፡


በአጠቃላይ በፕሮጀክቱ 101 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የታቀፉ ሲሆን በ5ቱ ዓመታት ለሚሰሩት ሰላምን የማስፈን ስራ 6.5 ሚሊዮን ዩሮ ወይም በብር ሲሰላ ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድቧል፡፡


ከዚህ የፕሮጀክት ገንዘብ ውስጥ ከ3.7 ሚሊዮን ዩሮ ወይም ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላዩን ለ75 የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሰላም ግንባታና ተያያዥ ስራዎቻቸው ድጋፍ ለማድረግ የታለመ ነው ተብሏል፡፡


ከዚህም ውስጥ በዛሬው እለት ለ36 ድርጅቶች ለእያንዳንዳቸው ከ6 ሚሊዮን ብር በላይ በድምሩ ከ230 ሚሊዮን ብር በላይ የድጋፍ ስምምነት ፕሮጀክቱን እንዲተገብሩ ሃላፊነት የተሰጣቸው 3 ድርጅቶች ከኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ጋር ተፈራርመዋል፡፡


ወ/ሮ ሳራ ወርቁ ፕሮጀክቱን ከሚተገብሩት ተቋማት መካከል የሆነው የቫልተር ሁንገር ሂልፌ (WHH) የተባለው የጀርመን የልማት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይ ናቸው፡፡


የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በመርሃ ግብሩ ባሰሙት ንግግር ከዚህ ቀደም መንግስትና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አብሮ ለመስራት የተመቸ አልነበረም ፣ ባለፉት 5 ዓመታት ተግባር ላይ በዋለው አዋጅ ተቀራርበው መስራት ችለዋል ብለዋል፡፡

የተፈጠረውን እድል እንዲጠቀሙበት ጠይቀዋል፡፡

ይሁንና የፋይናንስ ችግር ያለባቸው በመሆኑ የሚገባቸውን ያህል እንዳይሰሩ እንዳደረጋቸው ጠቅሰዋል፡፡


በፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ከተደረገላቸው ሃገር በቀል ድርጅቶች መካከል 22ቱ አዲስ የተቋቋሙ ናቸው ከእነዚህም መካከል አንዱ የዶክተር አምባቸው ፋውንዴሽን አንዱ ነው፡፡


የፋውንዴሽኑ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሮ መአዛ አምባቸው በፕሮጀክቱ ሊከውኑ ስላሰቡት ይህንን ብለውናል፡፡


ፋውንዴሽኑ ከተቋቋመ 2 ዓመት እንደሆነው ያነሱት ሃላፊዋ የተደረገላቸው የገንዘብ ድጋፍ በአማራ ክልል በገጠር ያሉ ሴቶችና ወጣቶችን የኢኮኖሚ አቅም ለማጎልበት ለሚሰሩት ስራ አጋዥ እንደሚሆን ነግረውናል፡፡


ይህ የ5 ዓመት ፕሮጀርክት እ.ኤ.አ ከ2023 እስከ 2028 የሚቆይ መሆኑንና የተደረገው ድጋፍ በትክክል ለታለመለት ዓላማ መዋል አለመዋሉን በኢትዮጵያ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በኩል ቁጥጥር እንደሚደረግበት ከምክትል ዳይሬክተሩ ከአቶ ፋሲካው ሰምተናል፡፡


ምንታምር ፀጋው

Comments


bottom of page