ጥቅምት 29፣2016 - ደን ለሰው ልጅ ብቻ ሳይሆን ለሌላውም ፍጡር ማረፊያ መሆኑን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠብቃ ያኖረቸው ለዚህ ማሳያ መሆኑ ተነገረ
- sheger1021fm
- Nov 9, 2023
- 1 min read
ደን ለአራዊቱም መጠለያና መጋቢ ለሌለውም ሌላውም ፍጡር ማረፊያ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠብቃ ያኖረቸው ደን ለዚህ ማሳያ መሆኑ ተነገረ፡፡
ይህን የተናገሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ናቸው፡፡
ፓትርያርኩ ይህን የተናገሩት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደን አጠባበቅን በተመለከተ በተዘጋጀ መድረክ ላይ ነው፡፡
ፓትርያርኩ የደን መመናመን በአለም አቀፍ ደረጃ እየተስተዋለ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት መሆኑ በግልፅ እየታየ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የደን መመናመንና መጥፋት እየታየ ስለሆነ አሁንም በስፋት ደንን መትከል ያሻል ያሉት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ያ ካልሆነ ግን አሁን ፍጥረት ሁሉ ለጎርፍ ፣ለድርቅና ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጡ መሆናቸው ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት ለውጥ በአለም አቀፍ ደረጃ ከሰብአዊ ፍጥረት ባለፈ በሁሉም መስክ ላይ የከፋ ችግር እያስከተለ ስለሆነ ከዚህ የባሰ ችግር ሳይመጣ ከወዲሁ በርትቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሳሙኤል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ደኖችን ነባር በሆነው ልምዷ ጠብቃ ኖራለች ፤ አሁንም እየጠበቀች ነው ብለዋል፡፡
ቤተ ክርስቲያኗ ለሰው ልጅ እና ለአራዊት መሸሸጊያ ብቻ ሳይሆን ለሀገር ብዙ የሚሰጡ ሀገር በቀል ዛፎችን ጠብቃ መኖሩን ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል አስታውሰዋል፡፡
በዚህም የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል በሚሰራው ስራ ቤተክርስቲያኒቱ የራሷ ድርሻ እየተወጣች ነው ብለዋል፡፡
በመካሄድ ላይ በሚገኘው የውይይት መድረክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የደንን ግንኙነት የተመለከቱ ጥናታዊ ፁፎች ቀርበውበታል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments