top of page

ጥቅምት 28፣ 2017 - ሕብረት ኢንሹራንስ ‘’በ2016 በጀት ዓመት የተጣራ 525.27 ሚሊዮን ብር አተረፍኩ’’ አለ።

ሕብረት ኢንሹራንስ ‘’በ2016 በጀት ዓመት የተጣራ 525.27 ሚሊዮን ብር አተረፍኩ’’ አለ።


ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲመሳከር ከግማሽ በላይ ወይም የ60.62 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።


#ሕብረት_ኢንሹራንስ ዓመታዊ የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባኤው በዛሬው እለት አካሄዷል።


ኩባንያው በበጀት ዓመቱ ከሁለቱም ዓብይ የመድን ዘርፎች(ከሕይወት እና ሕይወት ነክ ካልሆነው) የሰበሰበው አጠቃላይ አረቦን ገቢ ወደ 1.96 ቢሊዮን ብር እንደሆነ ጠቅሷል።


ከተሰበሰበው አጠቃላይ #አረቦን መጠን ብር 1.7 ቢሊዮን ብር የተገኘው ሕይወት ነክ ካልሆነ የኢንሹራንስ ስራ መሆኑ በሪፖርቱ ተመልክቷል።


የሕብረት ኢንሹራንስ የተከፈለ ካፒታል አንድ ቢሊዮን ብር መድረሱንና የኩባንያው ካፒታሉ ከባለፈው ዓመት በ221 ሚሊዮን ብር እድገት ያሳየ ሲሆን በአንድ አክሲዮን ያስመዘገበው ትርፍ አምና ከነበረው 47.99 በመቶ ወደ 53.21 በመቶ ከፍ ማለቱ ተጠቅሷል።


ባሳለፍነው ዓመት #የኢንሹራንስ_ኢንዱስትሪው በአማካይ 23.72 በመቶ እድገት ማሳየቱን የጠቀሰው ኩባንያው በዚህም የሕብረት ኢንሹራንስ እድገት 30.19 በመቶ መሆኑንና ኩባንያው በበጀት ዓመቱ 693 ሚሊዮን ብር ካሳ መክፈሉን ጠቁሟል።

ይህም ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ49.57 በመቶ ጭማሪ ያሳያል፡፡


በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት የኢንሹራንስ ኢንደስትሪው በርካታ ችግሮች እንደነበሩት አስታውሷል፡፡


ግጭቶች የሰዎችን እንቅስቃሴ በመገደብ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ማስከተላቸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የዋጋ ግሽበት፣ የኢትዮጵያ ብር ከዓለም ዋና ዋና ከሚባሉ ምንዛሬዎች አንጻር ያለው የመግዛት አቅም ማሽቆልቆል፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረት፣ በኢንቨስትመንቱ ረገድ የተፈጠረው ጉልህ የሆነ መቀዛቀዝ፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እና የባንክ ብድር መገደብ ወይም እንደሚፈለገው አለመሆን ባሳለፍነው በጀት ዓመት በሀገሪቱ ለተከሰተው አጠቃላይ የኢኮኖሚና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንዲያዘግሙ ካደረጉ ዓይነተኛ ችግሮች ዋና ዋናዎቹ ተጠቃሽ ምክንያት ናቸው ሲል ኩባንያው አሳውቋል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው ፉክክር በኢንደስትሪው አልፎ አልፎ የሚታየው ስነ ምግባር የጎደለው የንግድ ስራ እንቅስቃሴ በዓመቱ ያጋጠሙ ተጨማሪ ፈተናዎች ነበሩ ተብሏል፡፡


ፋሲካ ሙሉወርቅ

Comentários


bottom of page