ወደ ውጪ በሚላክ ጫት ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ህገ ወጥ ተግባራትን ለመከላከል መንግስት የተለያዩ እርምጃዎች መውሰድ መጀመሩን ተናገረ።
በዚሁ መሠረት በጫት ላኪነት የንግድ ፍቃድ ዘንድሮ ጭምር ያወጡት ዳግም ምዝገባ እንዲያከናውኑ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።
በጫት ንግድ የተሰማሩ አዲስም ሆኑ ነባር ነጋዴዎች የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያዘጋጀውን መስፈርት ማሟላታቸው እየተረጋገጠ እና ግዴታ እየገቡ ፍቃድ ይወስዳሉ ተብሏል።
ለዳግም ምዝገባው የሚኖራቸው ጊዜ እስከ ህዳር 15 /2016 ድረስ እንደሚሆን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ገብረመስቀል ጫላ ተናግረዋል።
በሀገር ውስጥ ያሉ እና ጫት በሚጓጓዝበት መስመር ያሉ ሁሉም ኬላዎች ሙሉ በሙሉ እንዲነሱ መወሰኑንም ይፋ አድርገዋል።
ሚኒስትሩ ዛሬ ከሠዓት በኋላ በመስሪያ ቤታቸው ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ወደ ውጪ በሚላክ ጫት ላይ የሚፈፀሙ ህገ ወጥ ተግባራት እየበዙ መጥተዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ወደ ውጪ ከሚላክ ጫት የምታገኘው ገቢ ከዓመት ዓመት እየቀነሰ ነው ብለዋል።
ለአብነትም በ2015 ወደ ውጪ ከላከችው ጫት የተገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ከ144 ሚሊዮን ዶላር በላይ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቅሰዋል።
ኮንትሮባንድን ጨምሮ የተለያዩ ህገ ወጥ ተግባራት ለዚህ ምክንያት መሆናቸውን ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ይህንኑ ለማስተካከል ሲባል ሁሉም ጫት ላኪ ነጋዴዎች በሚቀጥሉት 15 ቀናት ዳግም ምዝገባ እንዲያደርጉ ተወስኗል ብለዋል።
ዳግም ምዝገባውን ያላከናወነ ጫት ላኪ ነጋዴ ፍቃዱ መሠረዙን ይወቀው ተብሏል።
ጫት ወደ ውጪ ለመላክ ፍቃድ ከወሰዱ ከ4991 በላይ ነጋዴዎች አምና ቢያንስ አንዴ የላኩት 486ቱ ብቻ እንደሆኑ በመግለጫው ላይ ሲነገር ሠምተናል።
አንዳንዶቹ ነጋዴዎች ፍቃዳቸውን ለሌላ ወገን በማስተላለፍ ያልተገባ ጥቅም እያገኙ ነው ተብሏል።
ኢትዮጵያ በ2013 ከጫት ወጪ ንግድ 402 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ፣ በ2014 392 ነጥብ 2ሚሊዮን ዶላር ፣ በ2015 ደግሞ 248 ነጥብ 2 ሚሊየን ዶላር ማግኘቷ ተነግሯል።
ንጋቱ ረጋሳ
የሸገርንወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comentarios