top of page

ጥቅምት 26 2018 - የውጪ ሀገራት ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • 7 days ago
  • 2 min read

የእስራኤሉ የኢነርጂ እና የመሰረተ ልማት ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን ወደ ጋዛው ጦርነት መመለሳችን አይቀርም አሉ፡፡


ዔሊ ኮኸን በጋዛ ወደ ጠንካራው ድብደባችን ለመመለስ የምንጠብቀው የሟች ታጋቾችን አስከሬን በሙሉ መረከብ ብቻ ነው ሲሉ ለአገራቸው ቻናል 7 ቴሌቪዥን መናገራቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡

ree

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቀደም ሲል ባቀረቡት ባለ 20 ነጥቦች የሰላም እቅድ በጋዛ አልፎ አልፎ ቢጣስም የተኩስ አቁም ስራ ላይ ውሏል፡፡


እቅዱ የተኩስ አቁሙን መዝለቅ የሚከታተል አለም አቀፍ አረጋጊ ሀይል በጋዛ እንዲሰፍር ይጠይቃል፡፡


ዔሊ ኮኸን ግን አለም አቀፍ ሀይል ቢሰፍር እንኳ ሐማስን ትጥቅ ማስፈታቱ አይሆንለትም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


የአገራቸው ጦር ግን ወደ ጋዛው ዘመቻ ተመልሶ ሐማስን ትጥቅ ማስፈታቱን በብቃት ማሳካት ይችላል ብለዋል ኮኸን፡፡



የአሜሪካ የቀድሞ ምክትል ፕሬዘዳንት ዲክ ቼይኒ ሕልፈት በሀላፊነት ዘመን ባልደረቦቻቸው በከፍተኛ ሐዘን እየተዘከሩ ነው፡፡


ቼይኒ ባደረባቸው የሳምባ ምች የጤና እክል በ84 አመታቸው ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው የተሰማው ከትናንት በስቲያ ነው፡፡


ዲክ ቼይኒ ከአሜሪካ ምክትል ፕሬዘዳንቶች መካከል ስመ ገናናው ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡


አሜሪካ አለም አቀፍ ፀረ ሽብር ዘመቻ ብላ ትጠራው በነበረ ክንውን ስማቸው በቀዳሚነት የሚነሳው ዲክ ቼይኒ እንደነበሩ መረጃው አስታውሷል፡፡


በኢራቅ የቀድሞን ፕሬዘዳንት ሳዳም ሁሴንን አስተዳደር ያስወገደው ዘመቻ ዋናው ፊት አውራሪ ቼይኒ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል፡፡


የዘመኑ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆርጅ ደብሊዩ ቡሽ በቼይኒ ሕልፈት አሜሪካ ታላቅ ባለውለታዋን አጣች ማለታቸው ተሰምቷል፡፡


ኢራቅን በማውደም እና ምስቅልቅል ውስጥ በመክተት ስማቸውን በክፉ የሚያነሱም አሉ፡፡


የዲክ ቼይኒ ከዚህ አለም በሞት መለየታቸው እንደተሰማ የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እየተውለበለበ መሆኑ ታውቋል፡፡



በታንዛኒያ ካለፈው ሳምንት ረቡዕ አንስቶ ተጥሎ የሰነበተው የሰዓት እላፊ ተነሳ፡፡


ከምሽት እስከ ንጋት የሚዘልቀው የታንዛኒያው የሰዓት እላፊ ስራ ላይ ውሎ የነበረው ከምርጫው እለት አንስቶ ሁከት በመቀስቀሱ እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡


በፕሬዘዳንታዊ ምርጫው ገዢውን CCM የፖለቲካ ማህበርን የወከሉት ሳሚያ ሱሉሁ አሸንፈዋል ተብለው ቃለ መሐላ በመፈፀም ከትናንት በስቲያ አዲሱን ሀላፊነታቸው ጀምረዋል፡፡


ታንዛኒያ ከምርጫ ነኩ ብጥብጥ እየወጣች ነው ተብሏል፡፡


ቀስ በቀስም ወደ መረጋጋቷ እየተመለሰች መሆኑ ተጠቅሷል፡፡


ትምህርት ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች ዳግም እየተከፈቱ መሆኑ ተሰምቷል፡፡


በምርጫ ነኩ ግጭት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ሲነገር ሰንብቷል፡፡



በሱዳን ሰሜናዊ ኮርዶፋን የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ሰድዶታል በተባለ አጥቂ ሰው አልባ በራሪ አካል/ድሮን/ በርካታ ሰዎችን ገደለ ተባለ፡፡


የድሮን ድብደባው የተፈፀመው ኤል ኦቤይድ ከተማ አቅራቢያ ቀብር በሚከናወንበት ስፍራ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የድብደባው ሰለባዎች በቀብር ላይ የታደሙ ለቀስተኞች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡


RSF በሰላማዊ ሰዎች ላይ በሚፈፀም እልቂት ስሙ እየጠፋ ነው፡፡


በኤል ኦቤይድ አቅራቢያው የቀብር ስፍራ ጥቃት ፈፅሟል ስለመባሉ ፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ እንዲህም ነው እንዲያ ነው አላለም፡፡


የሱዳን መንግስት ጦር እና RSF ጦርነት ውስጥ ከገቡ ከ2 አመት ከመንፈቅ በላይ ሆኗቸዋል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

👇👇👇


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page