በኢትዮጵያ ግጭትና መፈናቀል ባለባቸው አካባቢዎች ያሉ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች ተደራራቢ ችግሮች የሚደርሱባቸው ቢሆንም በመንግስት ትኩረት ተነፍጓቸዋል ተብሏል፡፡
ግጭቶች በሚያስከትሉት ውድመት ከቤት ንብረታቸው ለሚፈናቀሉ ሰዎች የእለት ደራሽ ምግብና ሌላውንም ድጋፍ እንደሚደረግ ይታወቃል፡፡
ይሁንና በግጭቱ ምክንያት ይሁን በሌላ አካል ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰዎች፤ ይህ ነው የሚባል ድጋፍ አይደረግም ሲባል ይደመጣል፡፡
በተለይም በእነዚህ አካባቢዎች ያሉ የተለየ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ መሆናቸው ቢታወቅም፤ በዚህ ላይ በሚሰሩ የረድኤት ተቋማትም ይሁን በመንግስት ተረስተዋል፤ ያሉን የፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ምህረት ንጉሴ ናቸው፡፡
የህክምና ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት እንደ አእምሮ እድገት ውስንነት ያሉ እክሎች በአንድ በኩል በተፈጥሮ ሊከሰቱ ይችላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ እናቶች በእርግዝና ወቅት ማድረግ ያሉባቸውን ጥንቃቄዎች ካለማድረግ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

በግጭት አካባቢዎች እናቶች ከእርግዝና ክትትል ጀምሮ ሌላውንም ዓይነት ጥንቃቄ ለመውሰድ ያሉበት ሁኔታ የሚፈቅድላቸው እንዳልሆነ ወ/ሮ ምህረት ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ አሁንም ድረስ የቀጠሉ ግጭቶች የአካል ጉዳተኞችን ቁጥር እንዲጨምር፣ አኗኗራቸውን እንደሚያከፋው እንገነዘባለን ያሉን በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ ማሞ ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ሚኒስቴሩ እየሰራሁ ነው ያለውን ነግረውናል፡፡
አቶ አለማየሁ ከሌሎች ተቋማት ጋር በጉዳዩ ላይ በቅንጅት እንሰራለን ከማለት ውጪ ስለሚያደርጉት የተለየ ድጋፍ አልነገሩንም፡፡
የአካል ጉዳትን በተመለከተ ማህበረሰቡ ያለው አመለካከት አልተቀየረም የሚሉት አቶ አለማየሁ በየተቋማቱ ለአካል ጉዳተኞች የተመቸ አገልግሎት መኖር አለመኖሩን ክትትል አድርገን እንዲያስተካክሉ ምክረ ሃሳብ እንሰጣለን ብለውናል፡፡
ሃላፊው ይህንን ቢሉም አሁንም ድረስ የአካል ጉዳተኞች የተለያዩ መገለሎችና ፆታዊ ጥቃቶች ጭምር እንደሚደርስባቸው የፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ምህረት ንጉሴ ነግረውናል፡፡
በኢትዮጵያ ከ5 ሚሊዮን በላይ የአእምሮ እድገት ውስነት ያለባቸው ሰዎች እንዳሉ ከሃላፊዋ ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
Comments