top of page

ጥቅምት 26፣2017 - ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የፈቀደችው የ738.2 ሚሊዮን ዶላር ብድር በፓርላማው ፀደቀ፡፡

ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የፈቀደችው የ738.2 ሚሊዮን ዶላር ብድር በፓርላማው ፀደቀ፡፡


ሁለቱ ሀገራት ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት #የብድር ስምምነቱን መፈራረማቸው ተሰምቷል፡፡


ብድሩ በኢትዮጵያ እና በደቡብ ሱዳን መካከል ያለውን የንግድ ትስስር ያጠናክራል የተባለ የመንገድ ፕሮጀክት ለመገንባት ይውላል ተብሏል፡፡


ከሁለቱ ሀገራት ድንበር ተነስቶ ወደ #ደቡብ_ሱዳን 220 ኪሎ ሜትር የሚገነባው መንገድም የኢትዮጵያ የስራ ተቋራጮች ይገነቡታል መባሉን የስምምነት ሰነዱ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ሲቀርብ ሰምተናል፡፡


ለግንባታው ማስፈፃሚያ ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ የወሰደችውን 738.2 ሚሊዮን ዶላር ብድር ካላት በዶላር በጥሬው፤ ከሌላት ደግሞ በጊዜው የነዳጅ ዋጋ ተሰልቶ በነዳጅ ትከፍላለች ይላል ስምምነቱ ፡፡

እንዲህ ያለው አሰራር በመሰረተ ልማት እጥረት ምክንያት የተለያዩ ምርትና #ሸቀጦችን ለመሸመት ኡጋንዳ ላይ ብቻ ጥገኛ ሆና ቆይታለች የተባለችው ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የተሻለ የንግድ ግንኙነትን እንዲኖራት ያደርጋል የሚል አስተያየት ከእንደራሴዎቹ ተሰጥቶበታል፡፡


#ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን የፈቀደችው ብድር የ4 በመቶ ወለድ የሚታሰብበት ሲሆን 5 ዓመት የችሮታ ጊዜን ጨምሮ በ10 አመት ተከፍሎ የሚጠናቀቅ እንደሚሆን ከስምምቱ ተመልክተናል፡፡


ደቡብ ሱዳን እጇ ላይ ዶላር ከሌለ በድፍድፍ ነዳጅ ብድሯን ስትከፍል እስከ ፖርት ሱዳን በራሷ አጓጉዛ ማድረስ እንዳለባት የብድር ስምምነት ሰነዱ ያስገድዳል፡፡


ይሁንና አሁን ሱዳን ያለችበት ጦርነት ምን ይዞ እንደሚመጣ አይታወቅምና በሌላም በተመቸ ወደብ እንዲደረስን ማስተካከያ እንዲደረግበት ከአባላቱ ተጠይቋል፡፡


በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ በሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር ድኤታው እዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) በጉዳዩ ላይ ከደቡብ ሱዳን ጋር ንግግር ይደረግበታል የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡


በብድሩ ይገነባል የተባለውን የደቡብ ሱዳን 220 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ሀላፊነቱን የወሰደው የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የብድር ስምምነቱ ከፀደቀበት ከዛሬ ጀምሮ ብቁ የስራ ተቋራጮችን በማዘጋጀት ለግንባታው ስንዱ ይሆናል መባሉን ሰምተናል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን

Comments


bottom of page