ጥቅምት 25፣2017 - አውሮፕላኖች በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ እንዲያርፉ የሚያደርግ መሳሪያ ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እየተተከለ ነው
- sheger1021fm
- Nov 4, 2024
- 1 min read
አውሮፕላኖች በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ እንዲያርፉ የሚያደርግ መሳሪያ ቦሌ አለማቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ውስጥ እየተተከለ ነው፡፡
ይህን ያለው የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለስልጣን ነው።
ከዚህ በፊት መሳሪያው ባለመገጠሙ ጭጋጋማ አየር በሚከሰትበት ወቅት በተለይ አዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ማረፍ የነበረባቸው አውሮፕላኖች ጎረቤት ሀገራት ሄደው ለማረፍ ይገደዱ ነበር፡፡
የኢትዮጵያ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪ ባለሞያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት አቶ ግሩምነህ መሰረት እንደነገሩን፤ አሁን ላይ ኢትዮጵያ እየተጠቀመችበት ያለው መሳሪያ አውሮፕላኑ ሙሉ ለሙሉ በመሳሪያ ታግዞ ብቻ እንዲያርፍ የሚያደርግ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህንን ችግር ለመፍታት ስራዎች መጀመራቸውን የተናገሩ ሲሆን ለዚህ አገልግሎት የሚሆነው መሳሪያ ተገጥሞ ወደ ስራ ሲገባ አውሮፕላኖች በጭጋገማ የአየር ሁኔታ ማረፍ እንዲችሉ ያደርጋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቬሽን ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ መንግስቱ ንጉሴ በበኩላቸው ባለፈው ክረምት በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ምክንት 40 አውሮፕላኖች አዲስ አበባ ቦሌ ኤርፖርት ማረፍ ሲገባቸው ሌላ ኤርፖርት ለማረፍ ተገደዋል ብለዋል፡፡

ይህ የሆነው አውሮፕላኖች በእንዲህ አይነት የአየር ፀባይ በመሳሪያ ብቻ ታግዘው የሚያሳርፈው ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ የነበራት ደረጃ 1 ነበር አሁን እየተተከለ ያለው ደረጃ 3 ሲሆን ይህም ፓይለቱ አውሮፕላኑን በመሳሪያው ብቻ ታግዞ እንዲያሳርፍ ያግዘዋል ብለዋል፡፡
አሁን ላይ የመሳሪያው ገጠማ እየተደረገለት ነው ያሉ ሲሆን በመጪው ክረምት ወደ አገልግሎት ለማስገባት ታቅዷል ተብሏል፡፡
መሳሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ መገጠሙ ከዚህ በፊት በረራዎች ወደ ሌላ ስፍራ ለማዘዋወር የሚወጣው የነዳጅ እና ጊዜ እንዲሁም ለኤርፖርት የሚከፈል ወጪ ለማዳን ያግዛል ተብሏል።
በረከት አካሉ
Comments