በኔፓል የደረሰ የመሬት ነውጥ በጥቂቱ 128 ሰዎችን መግደሉ ተሰማ፡፡
ኔፓልን የመታው ርዕደ መሬት እጅግ ከባድ ነበር ተብሏል፡፡
ንቅናቄው እስከ ጎረቤት ህንድ ርዕሰ ከተማ ኒው ዴልሂ ድረስ መሰማቱን CNA ፅፏል፡፡
በርዕደ መሬቱ ከባድነት የተነሳ የአደጋው ሟቾች ብዛት ከተጠቀሰውም በእጅጉ ሊጨምር ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡
ኔፓል የመሬት ነውጥ የሚደጋገምባት አገር ነች፡፡
ከ8 አመታት በፊት በአገሪቱ የደረሰ ነውጥ ከ9 ሺህ በላይ ሰዎችን መግደሉን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የዚያን ጊዜው ርዕደ መሬት መጠነ ሰፊ የቁሳዊ ንብረት ውድመት አስከትሏል ይባላል፡፡

በኢራን በአንዱ የሱስ ማገገሚያ ማዕከል የተቀሰቀሰ ቃጠሎ በጥቂቱ 27 ሰዎችን ገደለ፡፡
በአደጋው ከ17 የማያንሱት ደግሞ የተለያየ ደረጃ ጉዳት ገጥሟቸው ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ዘ ኦብዘርቨር ፅፏል፡፡
አደጋው የደረሰው ከርዕሰ ከተማዋ ቴሕራን ሰሜናዊ ምዕራብ በ200 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኝ ከተማ መሆኑ ታውቋል፡፡
ቃጠሎው የተቀሰቀሰበት ምክንያት ለጊዜው አልታወቀም ተብሏል፡፡
የማዕከሉ የስራ ሀላፊዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው እየተጣራ መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
አደጋ የገጠመው ማዕከል የአደገኛ እፅ ሱሰኞች ማገገሚያ ሆኖ ሲያገለግል መቆየቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የእስራኤል ጦር ከሊባኖስ ጋር በምንዋሰንበት ድንበር አካባቢ የተጠንቀቅ ደረጃዬን እጅግ በጣም ከፍ አድርጌያለሁ አለ፡፡
የእስራኤል ጦር የተጠንቀቅ ደረጃውን ከፍ ያደረገው የሊባኖሱ የጦር ድርጅት /ሔዝቦላህ/ መሪ ሐሰን ናስረላህ ትናንት በቤይሩት በተካሄደ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ንግግር ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ናስረላህ በንግግራቸው በወር ገደማ በፊት የፍልስጤማውያኑ የጦር ድርጅት /ሐማስ/ በእስራኤል ላይ የፈፀመውን ድንገት ደራሽ ጥቃት ማወደሳቸው ተሰምቷል፡፡
በሐማስ ጥቃት ከ1,400 ያላነሱ እስራኤላውያን መገደላቸው ይነገራል፡፡
የሐማስን ጥቃት ተከትሎ እስራኤል በጋዛ በምትፈፅመው የአፀፋ ጥቃት ከፍተኛ እልቂት እያደረሰች ነው ተብሏል፡፡
የናስረላህን ንግግር ተከትሎ የእስራኤል ጦር ቃል አቀባይ ሔዝቦላህም በጋዛው ጦርነት ተደራቢ እሆናለሁ ካለ ውርድ ከራሳችን ብለዋል፡፡
በእስራኤል ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን በጋዛ የሰላማዊ ሰዎችን ስቃይ ለመቀነስ የእስራኤል ጥቃት እንዲለዝብ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ ሐማስ ከ200 በላይ ታጋቾችን ካልቀቀ የተኩስ አቁም ብሎ ነገር አይታሰብም ማለታቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርንወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comentarios