top of page

ጥቅምት 22፣2017 - አካል ጉዳተኞችን የተመለከተ አዋጅ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲፀድቅ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ይላካል ተባለ

ከተዘጋጀ ከሁለት ዓመታት በላይ የሆነው አካል ጉዳተኞችን የተመለከተ አዋጅ በሶስት ወራት ጊዜ ውስጥ እንዲፀድቅ ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ይላካል ተባለ፡፡


በቅርቡ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው #የአካል_ጉዳተኞች_አዋጅ የአካል ጉዳተኞችን መብት የሚጥሱ ግለሰብና ተቋማትን በህግ ተጠያቂ ሊያደርግ የሚችሉ ድንጋጌዎችን የያዘ ነው ተብሏል፡፡


ይህንን ያለው ረቂቁን ከማዘጋጀት ጀምሮ ዝርዝር መመሪያ የማውጣትና ተፈፃሚነቱን የመከታተል ኃላፊነት ያለበት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ነው፡፡


በሚኒስቴሩ የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ ማሞ የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ያስከብራል በሚል ተዘጋጅቶ ለዝርዝር እይታ ለፍትህ ሚኒስቴር የተላከው ረቂቅ አዋጅ ከ3 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ እንዲፀድቅ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚላክ ለሸገር ራዲዮ ተናግረዋል፡፡


አቶ አለማየሁ እንደሚሉት ሚኒስቴሩ የአካል ጉዳተኞችን #መብቶች ለማስጠበቅ የሚሰራቸው ውጤታማ የማሆኑት አካል ጉዳትን መሰረት አድርገው አድሎ የሚፈጽሙት የሚጠየቁበት የህግ አግባብ ባለመኖሩ ነው፡፡


አዲሱ ተቂቅ ህግ ይህንን ክፍተት ይሞላል ብለዋል፡፡


አካል ጉዳተኞች በስራ ቅጥር ወቅት አድልዎ ይደርስባቸዋል፤ በትምህርት ቤትም እንዲሁ በተለይ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ተማሪዎችን ብዙ ትምህርት ቤቶች ለመቀበል ፍቃደኛ እንደሚሆን ሲነገር ይደመጣል፡፡


ረቂቅ ህጉ እነዚህንና መሰል አካል ጉዳተኞች የሚደርሱባቸውን በደሎች በመዘርዘር እነዚህን በደሎች የሚያደርሱባቸው ተቋማትና ግለሰቦች በህግ ተጠያቂ የሚሆኑበት ድንጋጌ ጭምር ማካተቱን በየሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ጉዳይ መሪ ስራ አስፈፃሚው አቶ አለማየሁ ማሞ ነግረውናል፡፡


በረቂቅ ህጉ ዝግጅት ላይ ከሚኒስቴሩ ጋር አብሮ ሲሰራ የነበረው #ፍቅር_ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበርም በተለይም የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ሰዎች የሚደርስባቸው በደል ከፋ በመሆኑ የእነርሱን መብቶች የሚያስጠብቁ ድንጋጌዎች እንዲካተቱ ማድረጉን ነግሮናል፡፡


የማህበሩ ስራ አስኪያጅ ወ/ሮ የሸዋጌጥ ክብረት በረቂቅ ህጉ የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸው ልጆች የውርስ መብታቸው እንዲጠበቅ የሚያደርግ ድንጋጌ መካተቱን አንስተዋል፤ በተጨማሪም እነዚህን ልጆች ትምህርት የሚከለክሏቸውን ትምህርት ቤቶች ተጠያቂ የሚያደርጉ፤ እንደሌላው አካል ጉዳተኛ ከቀረጥ ነፃ ወደ ሃገር ቤት እቃዎችን እንዲያስገቡ የሚፈቅድና መሰል ድንጋጌዎች እንዲካተቱ አድርገናል ይላሉ፡፡


ፍቅር ኢትዮጵያ የአእምሮ እድገት ውስንነት ብሄራዊ ማህበር የአእምሮ እድገት ውስንነት ልጆች ባላቸው ወላጆች የዛሬ 30 ዓመት በ1987 ዓ.ም የተመሰረተ ማህበር ነው፡፡


ማህበሩ በእነዚህ ዓመታት አዲስ አበባን ጨምሮ በ9 ክልሎች ባሉት 17 ቅርንጫፎቹ ለ15 ሺህ ህፃናት የህይወት ክህሎት ስልጠናዎችን በመስጠት ካሉበት ችግር እንዲያገግሙ ማድረግንና በአሁኑ ወቅትም 150 በዚህ እክል ውስጥ ያሉ ሰዎችን እየደገፍኩ ነው ብሏል፡፡


ማህበሩ 30ኛ ዓመቱን ምክንያት በማድረግ ከፊታችን ሰኞ ጥቅምት 25 እስከ ዓርብ ጥቅምት 29 2017 ዓ.ም በኢትዮ-ኩባ ወዳጅነት አደባባይ በማሰናዳው ኤግዚብሽን ላይ በመገኘት የአእምሮ እድገት ውስንነት ኖሮባቸው አሁንም ድረስ በቤት ውስጥ የተቀመጡ ልጆች ያሏችሁ ወላጆች፣ ልጆቻችሁን ይዛችሁ ኑ እንቀበላችዋለን ተብላችኋል፡፡


ምንታምር ፀጋው

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page