የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት፤ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ስርቆትና በግንባታ ወቅት የሚደርስ ጉዳት ለስራዬ በብርቱ እንቅፋት ሆኖብኛል አለ፡፡
ስርቆት የሚፈፀመው በብዛት በአዲስ አበባ ከተማ መሆኑንም ለሸገር ተናግሯል፡፡
በበጀት ዓመቱ 3 ወራት ብቻ ከ2.7 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ባላቸው መሰረተ ልማቶች ላይ #ስርቆት ተፈፅሞብኛል ብሏል፡፡
ባለፈው ዓመትም የአሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ በተፈፀመ 155 የስርቆት ወንጀል ከ52.6 ሚሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሶብኛል ብሏል ተቋሙ፡፡

በወንጀሎቹ ተሳትፈዋል ተብለው ጥፋተኝነታቸው የተረጋገጠባቸው 57 ሰዎች ከአምስት ወር እስከ 18 ዓመት #እስራት ተፈርዶቸዋል ተብሏል፡፡
በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በተገዙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀም ስርቆት ከ5 ዓመት እስከ 20 አመት በደረሰ ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑም አገልግሎት ሰጭ መ/ቤቱ አስታውሷል፡፡
የብዙሃኑን ጥቅም በሚጎዳ መሰል ስርቆት ላይ የተሰማሩትን ህብረተሰቡ ሃይ በማለት እና እንዲያጋልጥ እንዲሁም ለ #ፀጥታ አካላት ጥቆማ እንዲሰጥ ጠይቋል፡፡
በሌላ በኩል የተለያዩ ተቋማት ግንባታ ሲፈፀሙ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ላይ ጉዳት እያደረሱ ነው ብሏል፡፡
ባለፉት 3 ወራትም ከ97,000 ብር በላይ ግምት ባለው ንብረቴ ላይ ጉዳት ደርሷል ብሏል፡፡
በዚህም ምክንያት አገልግሎት የሚቋረጥበትና የሚንገላታ የህብረተሰብ ክፍል ብዙ በመሆኑ ገንቢዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
Comments