top of page

ጥቅምት 20፣2017 - ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ሀያላን ሀገራት የሚጣልባቸው ካሣ እንዲከፍሉ በህግ ለማስገደድ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተነገረ

ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተያያዘ ሀያላን ሀገራት የሚጣልባቸው ካሣ እንዲከፍሉ በህግ ለማስገደድ የሚያስችል ስራ ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩን ተነገረ፡፡


ይህ የተባለው የክርስቲያን በጎ አድራጎት እና ልማት ማኅበራት ህብረት እያደረገው ባለው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ ነው፡፡


የህብረቱ ዋና ዳይሬክተር ንጉሱ ለገሰ(ዶ/ር) የጀርመን መንግስት በማደግ ላይ ካሉ ሀገራት ጋር በመሆን ሀያላን ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚጣልባቸው ካሳ በህግ እንዲከፍሉ ለማድረግ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡


በዚህ እንቅስቃሴ ላይ ኢትዮጵያ ጨምሮ ብራዚል ህንድ እና ሌሎች በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት አብረው እየሰሩ መሆኑን ሰምተናል፡፡


ዶክተር ንጉሱ ይህንን ለማስፈፀም ሀገራቱ አሁን እየመከሩ ነው ያሉ ሲሆን በተለይም በዓለም አቀፉ የፍትህ ፍርድ ቤት ካሣ አንከፍልም የሚሉ ሀገራትን ለመጠየቅ አቅደን እየተንቀሳቀስን ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡


በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት በከፍተኛ ደረጃ ጉዳት እየገጠማቸው ነው የሚሉት ዶክተር ንጉሱ በዚህም ምክንያት ገበሬው ችግር ውስጥ እየገባ ነው ለዚህም የክርስቲያን በጎ አድራጎት እና ልማት ማህበራት ህብረት ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ነው ብለዋል፡፡


የኢትዮጵያ አብዛኛው የምግብ ፍላጎት የሚያሟላው ገበሬው መሆኑን ይታወቃል የሚሉት የክርስቲያን በጎ አድራጎት እና ልማት ማኅበራት ህብረት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ንጉሱ ለገሰ የህዝብ ቁጥራችን በየጊዜው እየጨመረ ነው በዛው ልክ አየር ንብረትን መቋቋም የሚያስችል እቅድ እንደ ሀገር ከወዲሁ መተግበር አለብን ሲሉም አሳስበዋል፡፡


የክርስቲያን በጎ አድራጎት እና ልማት ማህበራት ህብረት እያደረገው ያለው ውይይት ጥቅምት 20 የሚጠናቀቅ ሲሆን በህንድና በብራዚል ወደፊት ይካሄዳል ተብሏል፡፡


ለአየር ብክለት ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ ሀገራት ካሣ መክፈል አለባቸው ይህም በህግ እንዲደገፍ ለማድረግ በማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በጋራ መስራት አለባቸው መባሉን ሰምተናል፡፡


በረከት አካሉ

Комментарии


bottom of page