ጥቅምት 20፣2017 - በሶማሊያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአማካሪነት የሚያገለግሉ አንድ ዲፕሎማት ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸው ተሰማ
- sheger1021fm
- Oct 30, 2024
- 1 min read
በሶማሊያ ሞቃዲሾ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ በአማካሪነት የሚያገለግሉ አንድ ዲፕሎማት በ3 ቀን ውስጥ ሀገሪቱን ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸው ተሰማ፡፡
መንግስታዊው የሶማሊያ የመገናኛ ብዙሃን ሶማሌ ደይሊ እንደዘገበው አሊ መሀመድ አዳን የተባሉ ዲፕሎማት ከሶማሌ እንዲወጡ የታዘዙት በሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መ/ቤት በኩል ነው፡፡
ትናንት በሚኒስቴር መ/ቤቱ ለኢትዮጵያው ዲፕሎማት የተፃፈው ደብዳቤ ሶማሊያ እርምጃውን የወሰደችው ብሔራዊ ጥቅሟን ለማስጠበቅ ነው ይላል፡፡
ዲፕሎማቱ የዲፕሎማሲ ስራን የማይመጥን ሌላ ስራ ውስጥ ተሳትፈዋል ሲል የሚከሰው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር መ/ቤቱ ጉዳዩን ግን አላብራራውም፡፡
የዲፕሎማሲን ስራ የማይመጥን ሲል የገለፀውን ፈፅመውታል ያለውን ተግባር በግልፅ ባያስቀምጥም ድርጊቱ የዲፕሎማሲ ግንኙነትን የሚመለከተውን የቪየና ኮንቬንሽንን የሚጥስ ነው ብሎታል፡፡
ዲፕሎማቱ ደብዳቤው ከደረሳቸው ሰዓት ጀምሮ በ72 ሰዓት ሶማሊያ ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸው በደብዳቤው ተጠቅሷል፡፡
ሶማሊያ የግዛቴ አካል ነች ከምትላት ሶማሌላንድ ጋር ኢትዮጵያ በወደብ ጉዳይ የመግባቢያ ሰነድ ከፈረመች ወዲህ ዲፕሎማሲያዊ ውጥረት ውስጥ መግባታቸው ይታወቃል፡፡
ትዕግስት ዘሪሁን
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Opmerkingen