''የ1997 የጋራ መሮሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች እና ሌሎች የ2005 እጣ ያልደረሳቸው የቤት ፈላጊዎች፤ እየተተገበሩ ባሉ የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች እያስተናገድኩ ነው'' ሲል የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ተናገረ።
ከተማ አስተዳደሩ፤ የ1997 ተመዝጋቢዎች ሆነው በወቅቱ በመረጃ ቋት ውስጥ ንቁ እና ብቁ የነበሩ ተመዝጋቢዎችን ሙሉ በሙሉ አስተናግዶ እንዳናቀቀ ተናግሯል።
ነገር ግን በወቅቱ ብቁ ያልነበሩትን የ1997 ተመዝጋቢዎች እና ሌሎች የ2005 እጣ ያልደረሳቸው የቤት ፈላጊዎች እየተተገበሩ ባሉ የተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች እያስተናገድኩ እገኛለሁም ብሏል፡፡
''ብቁ እና ንቁ'' ማለትም የቤት ፈላጊዎች በገቡት ግዴታ መሰረት የቁጠባ መጠን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በትክክል ተቀማጭ ማድረጋቸውን ማረጋገጥ ማለት እንደሆነም አስረድቷል።
ይህም የሚረጋገጠው እጣ ከመውጣቱ በፊት መሆኑንም ቢሮው ጠቅሷል።
የ1997 የጋራ መኖርያ ቤት ተመዝጋቢዎችን በተመለከተ ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለው መረጃ ከአውድ ውጪ ተተርጉሟል ብሏል።

በወቅቱ ብቁ እና ንቁ ያልነበሩ የ1997 ተመዝጋቢዎች ከየትኛውም የቤት ልማት መርሃ ግብር ውጪ እንደተደረጉ ተደርጎ የተሰራጨው መረጃም ሀሰት ነው ብሎታል።
መረጃው ልክ እንዳልሆነም ህብረተሰቡ ይገንዘብልኝ ሲል ተናግሯል።
ቢሮው ከአውድ ውጪ ተተርጉሟል በማለት ጉዳዩን ለማብራራት በማህበራዊ የትስስር ገጹ ባሰፈረው መረጃ ''ሀሰተኛ መረጃ የሚያሰራጩትን ከተማ አስተዳደሩ በህግ የሚጠይቅ ይሆናል'' ብሏል።
የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት እና አስተዳደር ቢሮ ከአውድ ውጪ ተተርጉሟል ያለው እና የ1997 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች በተመለከተ ተሰራጨ ያለው መረጃ መቼ እና በማን በኩል የተነገረ እንደሆነ አልጠቀሰም።
ነገር ግን የከተማዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከቀናት በፊት የ1997 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢዎች በተመለከተ ከፖለቲካ ፖርቲ ተወካዮች ጥያቄ ተነስቶላቸው ምላሽም መስጠታቸው ይታወሳል።
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments